ሀገራዊ ምክክር ሰላማዊ መፍትሄ በሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለማካሄድ የታሰበው ሀገራዊ ምክክር ሰላማዊ መፍትሄ በሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ ዕድል የሚሰጥ ነው መሆኑ ተገለጸ፡፡
የሀገራዊ ምክክሩ አካል የሆነው የቅድመ ምክክር መድረክ በሲዳማ ክልል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።
በሀዋሳ ከተማ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰቢያ የተሳታፊዎች ልየታ ላይ ምክክር እየተደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ እንደገለፁት በሂደት ላይ ያለው የምክክር መርሃግብር በኢትዮጵያ ሰላማዊ መፍትሄ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲመጣ ዕድል ይሰጣል።
መመካከርን ባህል በማድረግ ልዩነትን በማጥበብ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠርም አወንታዊ ሚና እንዳለው ኮሚሽኑ ያምናል ብለዋል።
አጀንዳውን በተመለከተ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ፊትለፊት ተገናኝቶ መመካከር አዳጋች ስለመሆኑ ጠቅሰው ይህን ችግር ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ለመወያየት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ተሳታፊዎቹም በንቃት እና በፍላጎት እየተሳተፉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው እንደ ሀገር እየገጠመን ያለው ችግር በስክነት ያለመነጋገር ችግር መሆኑን ጠቅሰው እንደ ሀገር የታቀደው ምክክር የተሻለ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ አለን ብለዋል።
ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ ኢትዮጵያን ከእነችግሯ ከማስረከብ ለመታደግ እንደሚረዳ ጠቅሰው የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል ብሩህ ለማድረግ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጋ በትጋት እና በቅንነት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ

More Stories
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ምክንያት በማድረግ የብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የምረጡን ቅስቀሳና ድጋፍ ሰልፍ በኣሪ ዞን ጋዘር ከተማ አካሄዱ
በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ እና በላሃ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ የማጠቃለያ ሕዝባዊ የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራም ተካሄደ
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን 7 ቀናት ብቻ ቀርተውታል