ኮሚሽኑ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው ለሚሳተፉ ተወካዮች ያዘጋጀው መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል
ሀዋሳ: ሰኔ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው ለሚሳተፉ ተወካዮች ያዘጋጀው መድረክ በሀዋሳ ከተማ ሚሊንየም አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል::
በችግሮቻቸው ዙሪያ ያልተመካከሩ ሀገራት ዛሬ በቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ናቸው::
ለዘመናት ሲንከባለሉ በመጡ በርካታ ጉዳዮች ጊዜ ሰጥተን ባለመመካከራችን አሁን ለሚስተዋለው አለመግባባቶች ምክንያት ሆነዋል ያሉት ኮሚሽነሩ አሁን ግን በውይይት ለችግሮቻችን መፍትሔ የምናበጅበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል::
የምክክር ሂደቱ ሁሉንም ያሳተፈ ሲሆን የሀይማኖት እና የባህል አባቶች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ምሁራንና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ከስሜት በፀዳ መንገድና ኢትዮጵያን በሚያሻግር መልኩ ሰፊ ምክክር ያደርጋሉ ብለዋል::
በዛሬው እለት ኮሚሽኑ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው ለሚሳተፉ ተወካዮች ባዘጋጀው መድረክ ላይ 3 ተወካዮች የሚመረጡ ይሆናል:: ከሚመረጡ ተወካዮች መካከል 2ቱ ዋና ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን አንድ ሰው ደግሞ ተጠባባቂ ይሆናል ተብሏል::
ተወካዮቹ የሚመረጡት ለእውነት ባላቸው አቋም፣ በእውቀት፣ በማህበረሰብ ዘንድ ባላቸው ተአማኒነት ላይ ተመስርቶ ይሆናልም ነው ያሉት ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ::
በሀዋሳ ከተማ በሁለት ማዕከላት ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 3 ሺ 600 ዜጎች በውይይት መድረኩ እየተሳተፉ ይገኛሉ::
ዘጋቢ: ማሬ ቃጦ

More Stories
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ ግንኙነትና አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር መሆኑ ተገለጸ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸዉ – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ
የሕዝባችንን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ የመመለስና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅ ቁርጠኝነታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)