ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና የምርምር ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ የህብረተሰብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ አስታወቀ
“የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለሁለተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በክልሉ የሚሰሩ የጥናትና የምርምር ውጤቶችን በማስመልከት የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በቡታጅራ ከተማ ተካሄዷል።
በክልሉ የሚገኙ ፀጋዎችን ለመለየትና ለማልማት የሚያግዙ የጥናትና የምርምር ስራዎችን በማዘጋጀት ወደ ተግባር ለመለወጥ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የነሱት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብላቱ ናቸው ።
በክልሉ የሚገኙ እምቅ የቱሪስት ፀጋዎችን በማልማትና በማስታወወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በቱሪዝም ዘርፉ የሚታዩ ውጤቶችን ለማሳደግና ውስንነቶችን ለመቅረፍ ያለማ የጥናትና የምርምር ስራ መከናወኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማልማትና ከመጠበቅ ባሻገር የማህበረሰቡን ወጎችና ልማዶችን የማጥናትና በየጊዜው የሚሰሩ የዕደ ጥበቡ ውጤቶችን በማስተዋወቅ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ የጥናትና የምርምር ስራዎች ከተከናወኑባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል።
በክልሉ በየዓመቱ የማህበረሰብ ጤና መድህን ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በዘርፉ የሚታዩ ውስንነቶችን ለመፍታት የጥናትና የምርምር ስራዎች አጋዥ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የክልሉ አመራር አካዳሚ በተለያዩ ጉዳዮች የጥናትና የምርምር ስራዎችን በማሠራት አቅጣጫዎችን የማመላከትና ተግባራዊነታቸውን የመከታተል ኃላፊነት እንደሚወጣ ያነሱት ደግሞ የክልሉ አመራር አካዳሚ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ዋና አስተባባሪ የሆኑት አቶ ከይረዲን ረህመቶ ናቸው ።
በተለያዩ ጊዜያት የሚሰሩ የጥናትና የምርምር ስራዎችን ወደ ተግባር በመቀየር የክልሉን የመልማት አቅም ከፍማድረግ እንደሚገባም አቶ ከይረዲን ጠቁመዋል።
በምክክር መድረኩ የቱሪዝም አቅምና የጥበብ ውጤቶች ለስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ውጤታማነትና የፋይናንስ አጠቃቀም በሚል ርዕስ የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ በየጊዜው በግለሰቦች፣ በተቋማትና በመንግስት የሚዘጋጁ የጥናትና የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር ተለውጠው የማህበረሰቡን ችግር እንዲቀርፉ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል።
በመድረኩም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብላን ጨምሮ የክልሉ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ተመራማሪዎች፣ጥናት አቅራቢዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል ።
ዘጋቢ:-ሙጂብ ጁሀር ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ቡድን በሚዛን አማን ከተማ አረንጓዴ አሻራ አሳረፉ
የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት 5ኛ አመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች እየተከበረ ነው
በክልሉ በተያዘው የበልግ ወቅት በኩታገጠም ሩዝና በቆሎ እያለሙ ያሉ አርሶአደሮች ተስፋ ሰጪ የሆነ የምርት ውጤት እንድናይ አስችሎናል አሉ።