አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በቅንጅትና በጥምረት መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ

አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በቅንጅትና በጥምረት መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ

የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከክልሉ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ”የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ “በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ የሚከባረው ዓለም አቀፍ አካል ጉዳተኞች ቀን በዓል በቡታጅራ ተከብሯል::

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሃሰን እንደተናገሩት አካል ጉዳተኞች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች የተጋለጡ ናቸው።መንግስት አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል ብለዋል::

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ መሐመድ ሻይቾ እንደተናገሩት የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማሳደግ ተሳትፏቸው እንዲያድግና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ሁሉም ኃላፊነቱን በተገቢው እንዲወጣ መክረዋል::

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ተፈጥሮ ሰዎችን በሁለት እንደሚከፍል ሁሉ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽንም አካል ጉዳተኛ እና አካል ጉዳተኛ ያለመሆን ዋስትና የሌላቸው ሰዎች በማለት ይመድባል ብለዋል::

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊና ማህበራዊ ዘርፍ ኃላፍ ወ/ሮ ሰርካለም ሳሙኤል እንደገለጹት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በአካቶ ትግበራ ላይ በአጽንኦት እየተሰራ ነው ብለዋል::

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሉምባ ደምሴ አካል ጉዳተኞች በህብረተሰቡ ውስጥ ስር ሰዶ በቆየ በተዛባ አመለካከት በቂ ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።

ከዚህም የተነሳ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ዘርፎች ከሌላው ህብረተሰብ ጋር እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ሳይሆኑ እንደቆዩ አንስተዋል::

የአካል ጉዳተኞችን በዓል ቀን ከማክበር በዘለለ አካል ጉዳተኞች የጤና፣የትምህርት፣የመረጃ እና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት ይሠራል ብለዋል የቢሮ ኃላፊው አቶ ሉምባ::

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ግዛቸው ዋሌራ በበኩላቸው አካል ጉዳተኝነት ከምንም ነገር ማስቆም እንደማይቻል በዓለም ላይ ታሪክ ከሰሩ አካል ጉዳተኞች ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል ብለዋል::

የሚመለከታቸው አካላትም የወጡ ህጎችን ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መስራት ይገባል ሲሉ አቶ ግዛቸው አሳስበዋል::

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በክልሉ በሁሉም ዘርፎች እየታዩ ያሉ ለውጦች አበረታች መሆናቸውን አንስተው ለዚህም የክልሉ መንግስት ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት የሰጠው ትኩረት አንዱ ማሳያ እንደሆነ አመለክተዋል።

ዘጋቢ፡በየነ ሰላሙ-ከሆሳዕና ጣቢያችን