አካባቢን በመጠበቅና በማጽዳት ምቹና ጽዱ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሁሉም የድርሻውን ልወጣ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ

አካባቢን በመጠበቅና በማጽዳት ምቹና ጽዱ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሁሉም የድርሻውን ልወጣ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ

“ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ” በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የተጀመሩ የጽዱ ኢትዮጵያ ዘመቻዎች በሁሉም አካባቢዎች ተጠናከረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

አካባቢን ማጽዳትና መንከባከብ የሁሉም ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሚ እንደ ሀገር በተጀመረው የንቅናቄ ስራ ከ15 ሚሊየን በላይ የህብረተረብ ክፍሎች በቀጥታ የሚሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመጀመሪያ ዙሪ “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የንቅናቄ መድረክ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የክልሉ ደን አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢንጂነር አስራት ገብሬማርያም በሪፖርት አቅርበዋል።

“ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ” በሚሪ ቃል የተጀመረው የንቅናቄ መድረክ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ይቀጥላል ብለዋል።

በከተሞች የቆሻሻ አወጋገድ ላይ የወጣ  ክልላዊ አዋጅ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በክረምት በጎ ፊቃድ አገልግሎት ባለፉት  ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትና የቀጣይ ስራ እቅድ በክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ በወ/ሮ ገነት መኩሪያ ቀርቧል።

በመድረኩ የተገኙ አካላት በበኩላቸው የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል የተያዘው እቅድ እንዲሳካ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።

በንቅናቄ መድረኩ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ : አካሉ ወልደኢየሱስ- ከቦንጋ ጣቢያችን