ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ

ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ: ሰኔ 25/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይግለጡ አብዛ ገለፁ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከክልሉ አመራር አካዳሚ ጋር በመቀናጀት በየደረጃው ለሚገኙ የፓርቲ አመራሮች ያዘጋጀው የስልጠና መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይግለጡ አብዛ እንደገለፁት ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን አገልግሎት በተገቢ ሁኔታ መስጠት እንዲቻልና የፖለቲካ ስራዎችም በአደረጃጀት እንዲተገበሩ በየደረጃው የሚገኙ ሁሉም የፓርቲ አመራሮች ወጥ አሰራሮችን ሊከተሉ ይገባል።

ስራዎች በመመሪያና ደንብ መመራት አለባቸው ያሉት አቶ ይግለጡ በዛሬው ዕለት ከ13 በላይ መምሪያዎች ላይ ለፓርቲ አመራሮቹ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

አመራሩ የተሻለ ግንዛቤ ይዞ ህብረተሰቡን በተገቢ ሁኔታ ማገልገል እንደሚገባ ጠቁመው እንደ ሀገር የተጀመሩ የልማት ውጥኖችን ከግብ ማድረስ እንዲቻልና በዚሁም የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ከሰራን ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን ያሉት አቶ ይግለጡ ለሁለንተናዊ የኢትዮጵያ ብልጽግና ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ያነጋገርናቸው የስልጠናው ተሳታፊዎችም በበኩላቸው ስልጠናው ለተቋም ግንባታ ብሎም ለአመራር ግንባታ ፈይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመው በያካባቢያቸው ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን