ሀዋሳ፡ ሰኔ 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተካሄደ በሚገኘው የሠላም፣ የአንድነት እና የልማት ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፥ ከሚለያዩን በላይ የሚያቀራርቡን፤ ከሚከፋፍሉን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን እና የሚያስተሳስሩን እጅግ ብዙ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
“ጠንካራ ክልላዊ አንድነትና አብሮነት ለዘላቂ ሠላምና ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው ኮንፍረንስ፥ ከመላው የክልሉ መዋቅር የተገኙ ከ1 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ክልሉ ከምስረታው ጀምሮ ያደሩ ጥያቄዎችንና የሕዝቡን አዳዲስ የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዚህም ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች መመዝገባቸውንም ጠቅሰዋል።
የህግ የበላይነትና ፍትሃዊነት የተረጋገጠበት ክልል እንዲሆን ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ በነበሩ ጊዜያት ከ 155 በላይ ልዩ ልዩ አዋጆችና የህግ ማዕቀፎች ፀድቀዉ ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።
በክልሉ የተረጋገጠው ሰላም ማህበረሰቡን የሰላም ታጣቂ በማድረግ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩንና የፀጥታ መዋቅሩን በማጠናከር የተገኘ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኮንፈረንሱ በክልሉ ግጭት እንዲመጣ የሚፈልጉ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚደረግበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በክልሉ የተረጋገጠውን ሰላም ለማፅናት የትኛውንም ልዩነት በንግግር የመፍታት ባህል የገነባ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚገባም አመልክተዋል።
በክልሉ ሕዝቦች መካከል ወንድማማችነ እንዲፀና ባለፉት ጊዜያት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተፈጠሩ ህፀፆችን በይቅርታ መሻገር እንደሚያስፈልግም ርዕሰ መስተዳድሩ አስምረዋል።
አብሮነትን በዘነጋና ከግል ፍላጎት በመነጨ አስተሳሰብ የተፈጠሩ ኩርፊያዎችና መቆሳሰሎች ለሕዝቡ ጥቅም ሲባል እንዲቀሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ፣ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ዶ/ር ተስፋዬ ቤልጅጌ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አልምጸሐይ ጳውሎስ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በኮንፈረንሱም ክልላዊ የምሁራን ፎረም በመመስረት፣ ክልላዊ የባህልና ቋንቋ ልማት አማካሪ ምክር ቤት እና የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ፎረም በማደራጀት ክልሉ አንድነቱን የማፅናት ስራ ይሰራል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
ከተማዋን ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር የሚያገናኝ የድልድይ መሠረተ ልማት ግንባታ እያካሄደ እንደሚገኝ የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር ውይይት አደረጉ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በክልሉ የቤተሰብ ቀንን ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ