በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም በክልሉ 8 ወረዳዎች በመንገድ ግንባታና ጥገና እንዲሁም ተንጠልጣይ ድልድይ፣ የተለያዩ የመንገድ ስትራክቸር ስራዎችን እየሰራ ይገኛል – መሀመድ ኑሪዬ (ዶ/ር)

ሀዋሳ፡ ሰኔ 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም በክልሉ 8 ወረዳዎች በመንገድ ግንባታና ጥገና እንዲሁም ተንጠልጣይ ድልድይ፣ የተለያዩ የመንገድ ስትራክቸር ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑሪዬ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልት ቢሮ የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና (RCFSP) ፕሮግራም ከስትሪግ ኮሚቴ አባላት ጋር የ2017 በጀት ዓመት የ12 ወራት ፕሮጀክት አፈፃፀምና የ2018 መነሻ ዕቅድ ላይ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ዉይይት እየተደረገ ነዉ፡፡

የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም በዓለም ባንክ ድጋፍና በክልሉ መንግስት በጀት የሚሰራ የመንገድ ልማት ዘርፍ መሆኑን የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊዉ፤ ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት በርካታ የመንገድ ስራዎችን በመስራት የሚታወቀዉ የሁሉ አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት (ዩራፕ) ተክቶ ፕሮጀክቱ በክልሉ 8 ወረዳዎች ተመርጠዉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም 36 ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ የዕቅድ አካል ተደርጎ መገባቱን የጠቀሱት ለስትሪግ ኮሚቴዉ መነሻ የዉይይት ሰነድ ያቀረቡት የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሁሉ አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ሎምበሶ፤ 123 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን 9 አዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት፣ 136 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን 13 የነባር መንገድ ጥገና ፕሮጀክት እንዲሁም 5 ተንጠልጣይ ድልድይ የሚሸፍን መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት የሆኑ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነዉ፡፡

ዘጋቢ፡ ድልነሳዉ ታደሰ