በጎፋ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አዘጋጅነት “የተሻሻለ የቤተሰብ ሥራና ገቢ ለሐገር ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ቃል ዞናዊ የቤተሰብ ቀን ምክክር መድረክ በሳውላ ከተማ ተካሂዷል

የጎፋ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ ቦራና ቦሎ፤ የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የአሰራር ስርዓትን ማጠናከር፣ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለመጨመር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው የቤተሰብ ቀን ሥራና ገቢ የተፈጠረለት የተሻለ ቤተሰብ ለመመሥረት ያለመ መሆኑን አመላክተዋል።

የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና የመንግሥት ረዳት ተጠሪ አቶ ይሁን ደምሴ፤ ሀገርን የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር የስነ-ምግባር ብልሹነትን ለማረም በኢኮኖሚና በአሰተሳሰብ ጠንካራ ቤተሰብ የመፈጠር ሥራ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የመምሪያው ማህበራዊ ደንነት ዋና ሥራ ሂደት አሰተባባሪ አቶ ዘርሁን ጊያ፤ በከተማና በገጠር የሥራ ልምምድን በማሻሻል በጠንካራ የሥራ ባህል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሰነድ አቀርበዉ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የጎፋ ዞን ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሀብታምነሽ ግራዝማች፤ ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት መጠበቅ፣ የቤተሰብ ሥራና ገቢ መጨመር ሀገር ለመገባንት ያለው ሚና የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች የሥራ ባህልን በማሳደግ በተለይ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ሰፊ ዕድል መኖሩን አንስተዋል።

ዘጋቢ፡ ሰንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን