በጎፋ ዞን የተፋሰስ ልማት ስራ ውጤት እያስገኘ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 25/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን በተከናወነ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም በተለይ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተጨባጭ ለውጦች መታየታቸው ተመልክቷል።

በዞኑ ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት አያያዝና አጠቃቀም ፕሮጀክት የተከናወኑ ስራዎች በፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ ጫንያለው፥ በዞኑ መሬትን በዘላቂነትት ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ለማዋል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ፕሮግራሙ በዞኑ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ አርሶ አደሩ በመሬት መራቆት የሚደርሰውን ጉዳት በመቀነስ፣ የመሬት ምርታማነትን በማበልፀግ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል።፡

የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መልካሙ ኡታ እንደገለጹት፥ በዞኑ በገዜ ጎፋና ኦይዳ ወረዳዎች በ31 ንዑስ ተፋሰሶች 10ሺ 141 አባ ወራ ተሳታፊ የሆነበትና ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 41ሺህ የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ስነ አካላዊና ስነ-ህይወታዊ ስራ በመስራት የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ መደረጉን የፕሮግራሙ አስተባባሪ ገልፀዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ዛፎች በመትከልና የፍራፍሬ ዛፎችን በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የቤተሰባቸውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዳስቻላቸው ገልፀው ፕሮግራሙ ባደራጀው ማህበር አባል የሆኑ አርሶአደሮች ቤተሰባቸውን በአግባቡ መመገብ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

የገዜ ጎፋ ወረዳ ግብርና ጸ/ቤትን ኃላፊ አቶ አይናለም ጾና በበኩላቸው፥ አርሶ አደሩ የግል ማሳዎችን ከአፈር መከላት በመጠበቅ ምርታማነታቸውን እንዲጨምር መሰራቱን አስታውሰዋል፡፡ ማምረት ተስኗቸው የነበሩ የወል መሬቶች ላይ በተሰራው የተፋሰስ ስራ ምርት መስጠት መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡ ይህም መሬቱ ከማገገም ባለፈ ለህብረተሰቡ የኢኮኖሚ ጥቅም እያስገኘ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ይህም በገጠር ለሚገኙ ወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር የራሱ ድርሻ ያለው መሆኑን አመላክተዋል፡፡

አርሶ አደር አማረ አሽነ የተራቆተው የአካባቢው መሬት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማልማት ከዚህ በፊት ከሚያገኙት የተሻለ እያመረቱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የክልሉ ዘላቂ መሬት አጠቃቀም ፕሮጀክት የአከባቢ ደህንነት ባለሙያ አቶ አለማየሁ ሶልባሞ፥ በወረዳው የተሰሩ ተግባራት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለመጨመርና ኑሮውን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ከመስክ ምልከታ መረዳታቸውን አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን