የባህል ፀጋዎቻችንን በአግባቡ መጠቀምና ማስተዋወቅ የአብሮነትን መሰረት ያጠናክራል – የኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

‎ሀዋሳ፡ ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የባህል ፀጋዎቻችንን በአግባቡ መጠቀምና ማስተዋወቅ የአብሮነትን መሰረት እንደሚያጠናክር የኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

‎ሚኒስቴሩ ከደቡብ ኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በአርባ ምንጭ ከተማ “ባህላዊ ሀብቶችን ለአብሮነት መጠቀም” በሚል ርዕስ ሲምፖዚየም እያካሄደ ይገኛል።

‎ሲምፖዚየሙ በሀገር ሽማግሌዎች የምርቃት ሥነ-ሥርዓት እና በጋሞ ዞን አስተዳደር የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ተጀምሯል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልማህዲ፤ “ሀገራችን የበርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መገኛ ናት፤ ትውልዶች በአንድነት ሀገራቸውን ጠብቀው አስቀጥለዋል። ዛሬም ይህንኑ አንድነትና መተባበርን አጠናክረን መቀጠል እንችላለን” ብለዋል።

‎”የኢፌዲሪ ህገ መንግሥትም ይህንን መርህ በግልጽ አስቀምጧል” ያሉት ሚኒስትሯ የባህል ዘርፍ ሀገራዊ አንድነትን፣ ወዳጅነትንና ወንድማማችነትን በማጠናከር ለትውልድ እንዲተላለፍ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

‎በተለይም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በባህላዊ ትስስር የበለጸገ በመሆኑ ይህንኑ መልካም አጋጣሚ ይበልጥ ለማጠናከር ይህ ሲምፖዚየም እንደተዘጋጀ ተናግረዋል።

‎በመድረኩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወይንቱ መልኩ በበኩላቸው፤ “ሀገራችን የብዙ ብሔሮችና ብሄረሰቦች መኖሪያ ናት፤ የጋራ ደም፣ ረጅም ታሪክና የቋንቋ ትስስርም አለን” ብለዋል።

‎ክልሉ የ32 ብሄሮችና ብሔረሰቦች መኖሪያ ሲሆን እነዚህ ብሄሮችና ብሔረሰቦች ከጥንት ጀምሮ በአንድነትና በመቻቻል እዚህ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።

‎ይህንን መልካም አብሮነት የበለጠ ማዳበር የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን ያሳሰቡት ኃላፊዋ፤ መንግሥትም ይህንኑ ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

‎ባህላዊ እሴቶቻችንን የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹ ሲሆን ይህ ሲምፖዚየምም የብሔረሰቦችን ወዳጅነት ለማጠናከርና አብሮነታችንን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

‎ለዚህ ሲምፖዚየም የውይይት መነሻ እንዲሆኑ የደቡብ ኦሞ፣ የኮንሶ እና የሀገር ሽማግሌዎች ፎረም ያዘጋጇቸው ሰነዶች ቀርበዋል።

‎ዘጋቢ፡ አማሮ አርሳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን