በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን የመምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን የመምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

ሀዋሳ፡ ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን የመምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ”ትውልድ በመምህር ይቀረጻል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ ቃል የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ፤ መድረኩ ሀገራዊ የመምህራን የምክክር አካል መሆኑን ጠቁመው በመምህራን እና በትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎችና አካላት የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ለውጤታማነት የሚያግዝ ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰነዱ ከቀረበ በኋላ በመምህራን በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ ውይይት ተደርጎ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚቀመጥ መሆኑንም ከንቲባው ጠቁመዋል።

የውይይት ሰነዱን እያቀረቡ ያሉ የሆሳዕና ከተማ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዱኔ፤ ትምህርት ሁሉ አቀፍ ዘላቂ ለውጥና ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ የቀጣይ ሀገር አደራን መረከብ የሚችል የሰው ኃይል የሚያፈራ በመሆኑ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በማድረግ ችግሮችን ለይቶ በመቅረፍ መፍትሄ ለማስገኘት የሚያግዝ የውይይት ሰነድ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመድረኩ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ፤ የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ዋና ተጣሪ አቶ ተሻለ ዶቦጭ፣ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዱኔ እና የከተማ አስተዳደር አመራር አካላት ሱፐርቨይዘሮች፣ መምህራን እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን