ሀገሪቱን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ተገለጸ

ሀገሪቱን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሀገሪቱን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር በማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማደረግ የብልፅግና ፓርቲ አመራርና አበላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ተመላክቷል።

“የመሀሉ ዘመን ወጥመድ መሻገር” በሚል መሪ ቃል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚዛን ክላስተር የብልፅግና ህብረት አበላት የውይይት መድረክ ተጠናቋል።

ለውይይት መድረኩ ሰነድ ያቀረቡት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የስልጠና ዘርፍ ኃላፊ እና የክላስተሩ ብልፅግና ፓርቲ ህብረት ሰብሳቢ አቶ ፀደቀ ከፍታው “የመሀሉ ዘመን ወጥመድ መሻገር” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው እና ከተረጂነት ለመላቀቅ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን የሚመለከት ፅሑፍ ለተሳታፊዎች አቅርበው ውይይት ተደረጎበታል።

ሀገሪቱን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚ በማድረግ በኩል የብልፅግና ፓርቲ ህብረት አመራርና አበላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባቸውም ተገልጿል።

በተለይም ክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና ፀጋ ያለው አከባቢ ከመሆኑም ባለፈ ያለውን ሀብት በአግባቡ በመለየትና በመምራት ሀገራችንም ሆነ ክልሉን ከተረጂነት እሳቤ ማውጣት እንደሚገባም ተጠቅሷል።

ሀገራችን እያሳየች ያለውን ለውጥና ዕድገት በህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሁም በስንዴ ምርት እየተመዘገበ ያለውን ውጤት በአሉታዊነት የሚያዩ አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉ አመራሩና አባላቱ በመረዳት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም የውይይት ተሳታፊዎቹ ገልፀዋል።

መንግስት የማይክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ ያደረገ ቢሆንም የመንግስት ሰራተኞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የኑሮ ውድነት ጫና እያሳደረ በመሆኑ ችግሮቹ የሚፈታበትን መፍትሄ ላይ በትኩረት ፓርቲው ሊሰራ እንደሚገባ ተመላክቷል።

ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር ተያይዞ የፌክ አካውንት አጠቃቀም፣ የነዳጅ ዕጥረት፣ ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ በተለይም ከሚዛን ቦንጋ እና ከታርጫ ጅማ ያለውን ህገ ወጥ የታሪፍ ጭማሪ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ በአጽንኦት ቀርቧል፡፡

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶችና በህክምና ዘርፍ ከወባ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ተገቢውን ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ እንዳለ ሁሉም ተገንዝቦ ትግል ሊያደረግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

ሁሉም የሀገሪቱንና የአከባቢውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብና በመረዳት ውስጣዊ ሆነ ውጫዊ ችግሮችን በመፍታት ዕጥረቶችን መድፈን እንዳለበት እና ከምርጥ ዘር ጥራት ጋር ተያይዞ የታየውን ችግር 5 ሺህ ኩንታል ዘር ወደ ካምፓኒው እንዲመለስ በማደረግ የመተካት ስራ መከናወኑን ወይዘሮ ሰብለ ወዳጆ የክልሉ ህብረት ስራ ኤጄንሲ ምክትል ዳይሬክተር ገልፀዋል።

በየደረጃው የተነሱ ዕጥረቶችን ለመቀረፍ የተቀናጀ አመራር ከማስፈለጉም ባለፈ በጉደለቶች ላይ አበላቱ ሳይሸነፍ ትግል ማድረግ እንዳለበትና ከፌክ አካውንት የሚዲያ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አይበራ አሰረድተዋል።

እንደ ክልል ከተረጂነት ለመላቀቅ በአደጋ ጊዜ የአንድ ቋት ማስቀመጫ ስርዓትን በመዘረጋት ከልመና መውጣት እንደሚያስፈልግ የገለፁት የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ህይወት አሰግድ የጠቅላይ ሚኒስተሩ ኢንሼቲቮች ኮሪደር ልማትን ጨምሮ በኑሮ ውድነት የሰንበት ገቢያን በማጠናከር፣ አጀንዳዎችን ለይቶ ህብረተሰቡን የማወያየት ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አብራርተዋል።

የመሀሉ ዘመን ወጥመድን አውቆ የመሻገር፣ የተሰሩ ስራዎችን አጎልቶ ማሳየት፣ ባለሙያው አመራሩና አበላቱ አገለግሎት ሰጪ በመሆን አምራቹና ሸማቾችን የማገናኘትና በአፈፃፀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን በጋራ መታገል እንደሚገባ ወይዘሮ ቤቴልሄም ዳንኤ የክልሉ ፕላንና ልማት የቢሮ ኃላፊ በምላሻቸው ገልፀዋል።

የውይይት መድረኩን ያጠቃለሉት በክልል ተቋማት የሚዛን ክላስተር የብልፅግና ህብረት ምክትል ሰበሳቢና የንግድና ኢንቨስትመንት ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ተስፋዬ እና የህብረቱ ሰብሳቢና የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፀደቀ ከፍታው እንደገለፁት ሀገራችን ፀንታ እንድትቆምና በባለፉት 7 ዓመታት የተመዘገቡ ለውጦችን አጠናክሮ ማስቀጠልና መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይ ፓርቲው የኢኮኖሚና የሰብዓዊ ልዕልና ይዞ እየሰራ ያለ በመሆኑ በሀገሪቱ ላይ ያለውን የፖለቲካ አውድን አመራሩና አበላቱ ተረድቶ ሊሰራ እንደሚገባም አቶ ፀደቀ ተናገረዋል።

በተለይም በየደረጃው ሀገሩን ፓርቲውንና ዜጋውን የሚጠብቅ አመራርና አበላት ሊፈጠር እንደሚገባ ሁሉም ተገንዘበው በየተሰማራበት የድርሻውን ሊያበረክት እንደሚገባም የህብረቱ ሰብሳቢው አስገንዘበዋል።

ዘጋቢ: አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን