በጋሞ ዞን በ2017 የምርት ዘመን 34 ሺህ 882 ሔክታር መሬት በበቆሎ ዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ

በጋሞ ዞን በ2017 የምርት ዘመን 34 ሺህ 882 ሔክታር መሬት በበቆሎ ዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ

‎በአሁኑ ወቅት በበቆሎ ሰብል ላይ የተከሰተውን ተምች ለመቆጣጠር የመንግሥት እገዛ እንደሚያስፈልጋቸውም የካምባ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

‎አርሶ አደር ሉቃስ አርአያ እና ገላነህ ተገኝ በጋሞ ዞን ካንባ ዙሪያ ወረዳ ማዜ ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው።

‎በ2017 ዓ.ም የምርት ዘመን ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ የግብርና ባለሙያዎች ትምህርት ወስደው ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ኩታ ገጠም መሬታቸውን በምርጥ ዘር በቆሎ በመሸፈናቸውና የአዝመራውም ቁመና ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ይናገራሉ።

‎የመሬቱ አቀማመጥ ለኩታ ገጠም እርሻ ምቹ በመሆኑ አርባ አርሶ አደሮች 50 ሔክታር መሬታቸውን ከእርሻ ዝግጅት እስከ አረም ቁጥጥር በጋራ ተጋግዘው በመሥራታቸው የተሻለ ምርት ለማግኘት እገዛው የጎላ መሆኑን ተናግረው፤ የአረምና የተባይ ቁጥጥር ሥራ በጋራ እያከናወኑ መሆናቸውንም አርሶ አደሮቹ ጠቁመዋል።

‎አልፎ አልፎ የተከሰተውን የበቆሎ ተምች ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የመንግሥት እገዛ እንዳይለያቸውም አርሶ አደሮቹ ጠይቀዋል።

‎በወረዳው የኦቶሎ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ነጋሽ ነፎ አርሶ አደሮች የግብርና ምክረ ሐሳብ ተቀብለው ምርታማ እንዲሆኑ የተጠናከረ እገዛ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

‎በወረዳው በአጠቃላይ 4 ሺህ 700 ሔክታር መሬት በዘር ከተሸፈነው ውስጥ 4 ሺህ 500 ሔክታር መሬት በበቆሎ ሰብል በኩታ ገጠም እርሻ በዘር መሸፈኑንና 197 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የተናግሩት ደግሞ የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሴሎ ይመር ናቸው።

‎በዞኑ 22 ሺህ 180 ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም እርሻ በቆሎ ለማልማት ታቅዶ በ107 ቀበሌያት 581 ክላስተሮች 22 ሺህ 882 ሔክታር መሬት በሙሉ ፓኬጅ መልማቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ማጌሶ ማሾሌ ተናግረዋል።

‎በበቆሎ ሰብል ላይ የተከሰተውን ተባይ ለማጥፋት በቅንጂት እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።

‎ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን