ሀዋሳ፡ ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከዛሬው ዕለት ጀምሮ እስከ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም ድረስ የሚሰጠው የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በይፋ መሰጠት መጀመሩን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡
ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ 59 ወራት ለሆኑ ህፃናት ክትባት ዘመቻውን ለመስጠት አቅዶ መርሃ-ግብሩን ይፋ መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትልና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ መና መኩሪያ ገልፀዋል።
በዚህም ከ1 ሚሊዮን 237 ሺህ 563 ህፃናት የክትባት አገልግሎቱን ያገኛሉ ሲሉም ሀላፊው አስረድተዋል።
ለህፃናት ክትባት ዘመቻውን መስጠት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያነሱት አቶ መና፤ በአሁን ወቅት እየተስተዋለ ያለው የወባ በሽታ ቁጥጥር ስራም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ዘመቻው የተሳካ ይሆን ዘንድ ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣና ዘመቻውን ከክልልና ከዞን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች ጋር በመሆን በይፋ አስጀምረዋል።
በመደበኛ አገልግሎት ያልተከተቡ እና ያቋረጡ ህፃናትን መለየትና መከተብ፣ የታመሙ ህፃናት ልየታና ወደ ጤና ተቋም መላክ፣ አጣዳፊ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ልየታና ወደ ጤና ተቋም መላክ፣ የቫይታሚን ኤ ጠብታ መስጠት፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትል ህክምና ኪኒን መስጠትና መሰል አገልገሎቶች ከዘመቻው ጎን ለጎን እየተሰጠ እንዳለም ተገልጿል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ እንደገለፁት፤ የእናቶችና ህፃናት ደህንነትና ጤናቸውን መጠበቅ በቅድመ መከላከል የጤና አጠባበቅ ዘዴ መሆን አለበት።
እንደ ዞን ከ65 ሺህ በላይ ህፃናት የክትባት ዘመቻውን እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል አቶ ማዕከል።
ዘመቻው በዞኑ የተሳካ እንዲሆን የዞኑ ሕዝብ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ጂንካ ዩንቨርሲቲ የመጀመሪያውን አለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ አካሄደ
በመስኖ ተቋማት ጥናትና ዲዛይን እና በግንባታ ተቋማት አስተዳደር ዘርፍ የተሻለ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመፍታት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ