የብልጽግና መንግስት ባለፉት አመታት የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር ጠንካራ የሆነ ስራ እየሰራ ነው – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)

ሀዋሳ፡ ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የብልጽግና መንግስት ባለፉት አመታት የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር ጠንካራ የሆነ ስራ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ።

በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ ከ41 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የ23 ኪሎ ሜትር የእናንጋራ -ተርሆኘ -ጋዛንቸ የጠጠር መንገድ ፕሮጀክት የምረቃ ስነስርኣት ተካሄዷል።

በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ.ር) እንደገለጹት፥ መንገድ አስፈላጊ ከሆኑ መሰረተ ልማቶች መካከል አንዱና ዋነኛው በመሆኑ የብልጽግና መንግስት ባለፉት አመታት የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በመጨረስና አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር ጠንካራ የሆነ ስራ እየሰራ ይገኛል።

የተመረቀው የእናንጋራ -ተርሆኘ -ጋዛንቸ የ23 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ሶስት ወረዳዎችን የሚያገናኝና የህብረተሰቡን የመንገድ ችግር የሚቀርፍ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ያለውን ተግባር ለማሳካት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ እንደገለጹት አሁን ያለንበት ጊዜ የህዝቡ ኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የጨመረበት ወቅት በመሆኑ በክልሉ የህዝቡን የመንገድ ጥያቄ ለመፍታት እየተሰራ ነው።

ለፕሮጀክቶች በተሰጠው ትኩረት ለረጅም ጊዜ ተጀምረው ያልተጠናቀቁና የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠሩ የነበሩ ፕሮጀክቶችን በመፈተሽ ደረጃ በደረጃ በመፍታት ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በመደበኛ የመንግስት በጀት የህዝቡ የመንገድ ፍላጎት ተደራሽ ማድረግ ስለማይቻል የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ በሁሉም አካባቢዎች የመንገድ ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው የጉራጌ ማህበረሰብ ከጥንትም ጀምሮ ለመንገድ መሰረተ ልማት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥና በዞኑ ያሉት ቀበሌያት ከገጠር መንገድ ጋር ማስተሳሰር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተያዘው በጀት አመት እስካሁን ባለው 400 ሚሊየን ብር ከማህበረሰቡ በማሰባሰብ 220 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱንም አስታወቀዋል።

በምረቃ ስነስርኣቱ ላይ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየትም ከዚህ በፊት በነበሩ ጊዜያት መንገድ ባለመኖሩ ምክንያት ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ይጋለጡ እንደነበረ አውስተው መንገዱ በመገንባቱ የእለት ተእለት ህይወታቸውን እንደሚያቀልላቸው ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ መላኩ ንማኒ – ከወልቂጤ ጣቢያችን