ከተማ አስተዳደሩ በተለያየ ስፖርት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማፍራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር ገለጸ

ከተማ አስተዳደሩ በተለያየ ስፖርት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማፍራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር ገለጸ

“ኢትዮጵያ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ-ቴኳንዶ አሶሴሽን” በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በከምባታ ዞን ሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር ሥልጠና እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥቷል፡፡

ሥልጠናው ወጣቱ ትውልድ የነገ ሀገር ተረካቢና በስነ ምግባር የታነፀ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ተወካይና የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሠመረ በላይነህ እንደገለፁት፤ ከተማ አስተዳደሩ በተለያየ ስፖርት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማፍራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

በተለይም በቴኳንዶና ውሹ ስፖርት ወጣቶች ከሀገር አቀፍ ደረጃ አልፈው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስንሻው ገ/ማርያም በበኩላቸው፤”ሌጀንድ ጂቲቲኤ” ሥልጠና ወጣቶቹ በአዕምሮና በአካል እንዲሁም በስነ-ልቦና ብቁ በማድረግ፣ በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

ሰልጣኞችም ከስልጠና በኋላ ህብረተሰቡን በተገቢ በማገልገል እና የባህርይ ለውጥ በማምጣት በዲስፕሊን መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ኃላፊው አመላክተዋል።

በመድረኩ የተገኙት የግራንድ ማስተር የዓለም ምክትል ፕሬዝደንትና አፍሪካ ቺፍ ዶ/ር ሄኖክ ግርማ በበኩላቸው፤ ማርሻል አርት በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በራስ የሚተማመን ወጣት ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

በስፖርቱ ዘርፍ የሺንሽቾ ከተማ ወጣቶቹ ለማደግና ለመለወጥ ያላቸው ፍላጎት ከስነ-ምግባር ጀምሮ የተሻለ እንደሆነ ዶ/ር ሄኖክ ገልጸዋል::

በመድረኩ ስልጠና የሰጡት ቺፍ ማስተር ኢንስትራክተር አልአዛር ተስፋዬ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ-አፍሪካ በመዘዋወር ስልጠናንና ግንዛቤን ማስጨበጫ በመስጠት ወጣቶችን እያበቃ ይገኛል።

ከሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከ120 በላይ ወጣቶችን በማሰልጠን ብቁ ማድረጋቸውንም ኢንስትራክተር አላዛር ገልጸዋል።

ካነጋገርናቸው ሰልጠኝ ወጣቶች መካከል ወጣት ፍቃዱ ዳንኤል እና ሳቦም ተመስገን፤ ስልጠናው በስነ-ምግባር እንዲታነፅ እንዳገዛቸው ጠቁመው ያገኙትን ግንዛቤ ተጠቅመው ሌሎች ታዳጊዎችን ለማሰልጠን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በማጠቃለያ መርሐ-ግብሩ የተለያዩ እንግዶችና ስልጠናውን የወሰዱ ወጣቶች የተለያየ ሰርተፊኬት እና ሽልማት ተበርክቷል።

ዘጋቢ: ደሳለኝ ታደሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን