በተለያዩ የግብርና ስራዎች የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲቻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ

በተለያዩ የግብርና ስራዎች የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲቻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ

በስልጤ ዞን ዋና አፈ-ጉበኤ ወ/ሮ መህዲያ ቡሴር የተመራ የዞኑ ምክር ቤት አባለት በዞኑ ሳንኩራ ወረዳ በመስኖ የለማ ማሳ ጎብኝተዋል።

በወረዳው በረግዲና ቆሬ እና ጃታ ቀበሌዎች የለሙ የበቆሎ ማሳ እንዲሁም በባህር ዛፍ ተይዞ የነበረን መሬት በሙዝ በመተካት እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

በጉብኝቱ ወቅት ለምክር ቤት አባላቱ ማብራሪያ የሰጡት የሳንኩራ ወረዳ አስተዳዳሪ ወ/ሮ ተሚማ ሙዴ፤ በወረዳው 559 ሄክታር መሬት በመስኖ መልማቱን ገልፀዋል።

በቆሎ፣ ድንች፣ የተለያዩ አትክልት፣ ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎችም ሰብሎች በመስኖ ከለሙት ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል።

በመስክ ጉብኝት ወቅት የተገኙት የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙበራ ከማል፤ አርሶ አደሩን በግብርናው ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

በሳንኩራ ወረዳ የብላቴ ወንዝን በመጠቀም የለማው የበቆሎ ማሳ ለዚህ ማሳያ ነው ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከመደበኛው የእርሻ ወቅቶች በተጨማሪ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎች እንዲለሙ በማድረግ በአመት ከሶስት ጊዜ በላይ በማምረት አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡት የምክር ቤት አባላት እንዳሉት፤ በሳንኩራ ወረዳ በመስኖ የለማ ማሳ ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው።

የምክር ቤት አባላት የህዝብ ተወካዮች በመሆናቸው በየአካባቢው ያለውን የውሃ አማራጭ በመጠቀም መስኖን በማልማት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ያለውን በማገዝ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በመስክ ጉብኝቱ የስልጤ ዞን ዋና አፈ ጉበኤን ጨምሮ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና እና የምክር ቤት አባላት በተገኙበት የችግኝ ተከላ ስራዎች ተሰርተዋል።

ዘጋቢ: አሚና ጀማል እና ሙጂብ ጁሃር – ከሆሳዕና ጣቢያችን