የካምባ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ቡናና ቅመማ ቅመም ማምረት በመጀመራቸው ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናገሩ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጋሞ ዞን የካምባ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ቡናና ቅመማ ቅመም ማምረት በመጀመራቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገለጹ።
በወረዳው 210 ሔክታር መሬት በቡናና ቅመማ ቅመም ምርት ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አስታውቋል።
ገዙሙ ጋጌ በወረዳው የጋርሣ ሐኒቃ ቀበሌ አርሶ አደር መሆናቸውን ጠቁመው፥ በ2 ሄክታር ማሣቸው ላይ የሐሪቲ ምርት የተከሉ ሲሆን ከ20ሺህ ብር በላይ እንደምያገኙ ነው የተናገሩት።
ምርቱ በቀበሌው ገና እየተለመደ መሆኑን የሚናገሩት አርሶ አደሩ፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርቱን እያስፋፉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አርሶ አደር አዶዬ ጾና በበኩላቸው በተለይም የአሪቲ ምርት ከሌሎች የግብርና ምርቶች ባሻገር ለአከባቢው አርሶ አደሮች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርቱ የማደጉን ያህል የገበያ ትስስር በቀጣይ የሚፈጠር ከሆነ የገቢ አቅማቸውን እንደሚያሳድግ ገልጸው የተሻለ የገበያ አማራጭ እንዲኖር ጠይቀዋል።
የካንባ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሴሎ ይመር እንደሚሉት በወረዳው 210 ሔክታር በቡናና ቅመማ ቅመም ለመሸፈን ከታቀደው ውስጥ 183 ሄክታር መሬት መሸፈኑን አስረድተው፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወረዳው እየተለመደ ያለው የአሪቲ ምርት የአርሶ አደሩን ትኩረት የሣበ በመሆኑ፥ 100 ሔክታር ማሳ በኩታ ገጠም ተከላ ተካሂዷል ብለዋል።
የአርሶ አደሩ የማምረት አቅም እንዲጨምር ሙያዊ ድጋፍ እየተደረ እንደሆነ ገልጸው ከማዕከላዊ ገበያ ጋር ትስስር ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አቶ ሴሎ አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡ ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ የሻይ ተክል ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ገለጹ
በተለያዩ የግብርና ስራዎች የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲቻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ
በሐመር ወረዳ ሲካሄድ የነበረው የህዝብ ለህዝብ እና የምሁራን ውይይት ተጠናቀቀ