በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ2 መቶ 93 ሺ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል – አቶ ሙስጠፋ ኢሳ

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ2 መቶ 93 ሺ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል – አቶ ሙስጠፋ ኢሳ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ2 መቶ 93 ሺ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ አስታወቁ።

ቢሮው በጉራጌና በየም ዞኖች እና በቀቤና ልዩ ወረዳ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው የሚሰሩ ማህበራት የስራ እንቅስቃሴን የመስክ ምልከታ አካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በመስክ ምልከታው ወቅት እንደተናገሩት፤ በክልሉ ባለፋት ዘጠኝ ወራት የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው 2 መቶ 93 ሺ ዜጎች መካከል ከ2 መቶ 23 ሺ በላይ የሚሆኑት ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።

ከተፈጠረው ቋሚ የስራ ዕድል መካከልም 41 በመቶው በግብርና ዘርፍ መሆኑን ያስታወሱት ሀላፊው፤ የምርት ሂደቱም ከተለመደው የመኸርና የበልግ እርሻ በመላቀቅ በመስኖ ስራ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

የመስክ ምልከታ ባካሄዱባቸው ቦታዎች ውጤታማ ስራ ማየታቸውን የተናገሩት አቶ ሙስጠፋ፤ ኢንተርኘራይዞቹ እያመረቱት ያለውን ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ገበያን ሊያረጋጋ የሚችል ነው ብለዋል።

በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች የወል መሬቶችን ለወጣቶች በማመቻቸት፣ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙና ሌሎችም ድጋፎች በማድረግ እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው መመልከታቸውንም ሀላፊው አክለዋል።

የጉራጌ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙራድ ያሲን፤ ለ52 ሺ ወጣቶች ቋሚ የስራ ዕድል በመፍጠር በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተደራጁ ማህበራት ከ2 መቶ ሚሊየን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ተመቻችቷል ብለዋል።

በዞን በአሁን ወቅት ወጣቶች በከፍተኛ ሁኔታ በግብርናው ዘርፍ እየተሰማሩ ይገኛሉ ያሉት አቶ ሙራድ፤ ይህም ለገበያ መረጋጋት ጉልህ አስተዋዕኦ እያበረከተ ይገኛል።

በበጀት ዓመቱ ከ4 ሺ 3 መቶ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ከ3ሺ 5 መቶ በላይ በቋሚነት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የተናገሩት የቀቤና ልዩ ወረዳ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሙዲን ሙዘሚል ናቸው።

በልዩ ወረዳው ያሉ የወል መሬቶች ለተደራጁ ወጣቶች በማስተላለፍ፣ ብድር በማመቻቸትና ግብዐቶችን የማቅረብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በጉራጌ ዞን ቸሀ እና እኖር ወረዳዎች እንዲሁም በቀቤና ልዩ ወረዳ ምልከታ ከተደረገባቸው ማህበራት መካከል ኬር፣ ቶሮት ይጣንሸና አሲን ሌሌንሳ ይገኙበታል።

የማህበራቱ ሰብሳቢዎች በሰጡት አስተያያትም መንግስት ባመቻቸላቸው ዕድል ተጠቅመው ከስራ አጥነት መላቀቃቸውን ተናግረዋል።

ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን በመጠቆም መንግስት ላደረገላቸው ድጋፍና ክትትልም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዘጋቢ: አስረስ ንጋቱ – ከወልቂጤ ጣቢያችን