ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ባለሙያዎች በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

ህብረተሰቡን በጤናው ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ህዝባዊ የውይይት መድረክ በወረዳው በሚገኙ ጤና ማዕከላት ተካሂዷል።

በወረዳው ከሚገኙ ጤና ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው በሐሩ ጤና ጣቢያ በመገኘት ዉይይቱን የመሩት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔ፤ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ባለሙያዎች በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን በወቅቱ ሲስተም ውስጥ አስገብቶ ከመምራት አንጻር የታዩ ጉድለቶችን ማረም እንደሚገባ ያሳሰቡት አስተዳዳሪው፤ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ በመስጠት የማህበረሰቡን የአገልግሎት እርካታ ለማረጋገጥ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የትርፍ ሰዓት አገልግሎት ክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ ከተገልጋዮችና ከባለሙያዎች በኩል የተነሱ ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን የተናገሩት አስተዳዳሪው፤ በወቅቱ በበጀት ውስንነት ክፍያ አለመፈፀሙን ገልፀዋል፤ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የባለሙያ ተነሳሽነት ለጤና አገልግሎቱ ውጤታማነት የላቀ ፋይዳ አለው ያሉት በወረዳው ጤና ጽ/ቤት ዕቅድ ዝግጅትና ግብረ መልስ ባለሙያ አቶ ገበየሁ ቦሮጂ፤ በአንዳንድ ጤና ባለሙያዎች የሚታዩ የሥነ ምግባር፣ የዕውቀትና የአመለካከት ችግሮችን በመፍታት ለተገልጋይና ለሙያው ክብር ሰጥተው ለሚሰሩ ባለሙያዎች ዕውቅና መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከሰራተኞች ጋር በችግሮች ዙሪያ በተደረገው ውይይት ግብዓት የሚሆን ሐሳብ መሰብሰቡን የገለፁት የሐሩ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ደግፌ፤ ርህሩህ፣ ተንከባካቢና ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ባለሙያ በመፍጠር የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በጤና ተቋማት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ የሚስተዋሉ ችግሮች ለተሻለ አገልግሎት በቀጣይ ሊስተካከሉ የሚገቡ ጉዳዮችንም አንስተዋል።

በወረዳው በሚገኙ ጤና ተቋማት ላይ ህዝባዊ ውይይት የተደረገ ሲሆን የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና ኃላፊዎች እንዲሁም ከማህበረሰቡ የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን