የመንገድ መሠረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት በቅንጅት መስራትን እንደሚጠይቅ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህብረተሰቡን የመንገድ መሠረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠይቅ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም የዘጠኝ ወራት ፕሮጀክት አፈፃፀም በቴክኒክ ኮሚቴ ለመገምገም ያዘጋጀው መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
ቢሮው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም ያከናውናቸው ተግባራት ሪፖርት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፥ ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ ከወረዳዎች መረጣ ጀምሮ እስከ ጨረታ ሂደት ያሉ ጉዳዮች ግልፀኝነትን የተላበሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሮጀክት ስራዉ አፈፃፀም የተሻለ ደረጃ ላይ መሆኑን የተናገሩት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላቱ በቀጣይ ጊዜ የቀሩ ስራዎችን ለማጠናቀቅ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል እና የሁሉ አቀፍ ገጠር ተደራሽ መንገድ ዘርፍ አስተባባሪ እንዲሁም የሪካፕ ፕሮግራም የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ማቲዎስ ሎምበሶ እንዳሉት የፕሮጀክት ስራው ከመጀመሩ ቀደም ተብሎ በአለም ባንክ ድጋፍ በሚሠሩ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ልምድ ካላቸው ተቋማት ተሞክሮ መውሰድ መቻሉ በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል አጋዥ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ለፕሮጀክቱ ስኬት የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ማቴዎስ በተለይ የፋይናንስ ቢሮና የግዥ ኤጀንሲ ድጋፍ ከፍተኛ ነው ብለዋል ።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በመድረኩ የተገኙት ሻምበል ጌጤ መለሰ በበኩላቸው በመንግስትም ሆነ በአጋር ድርጅቶች ለሚከናወኑ ስራዎች ስኬታማነት ቢሮዉ የሚያደርገውን ቅንጅታዊ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ፣ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ፣ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የሪካፕ ፕሮግራም ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር መሐመድ ኑርዬ፣ በመድረኩ ማጠቃለያ እንዳሉት የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራምን ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል ።
በበጀት ዓመቱ በክልሉ ፕሮጀክቱ ተግበራዊ በሚደረጉ 8 ወረዳዎች የአንድ መቶ አስራ አንድ ነጥብ 5 ኪሎሜትር የመንገድ ግንባታ ስራ በፕሮግራሙ የሚከናወን መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር መሀመድ ይህም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት በብዙ መልኩ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል ።
ስራዉ ውጤታማ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል ።
የመንገድ ስራ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የክረምት ወራት ሳይገባ ውል የተገባባቸው ሳይቶች ላይ በታቀደላቸው ጊዜና ጥራት ስራዎች እንዲጠናቀቁ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ዶ/ር መሀመድ አሳስበዋል።
ከግምገማ መድረኩ ማጠቃለያ በኋላ በሀዲያ ዞን ሚሻ ወረዳ የ29 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና አካል የሆነውን የ18 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገናና የግብዓት ማምራቻ ሂደትን የቢሮዉ አመራሮች፣ የሪካፕ ፕሮግራም ስትሪንግና ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ቀልጣፋ የመንገድና ትራንስፖርት አገልግሎት በለለበት ልማትን ማሳለጥ የሚቻል ባለመሆኑ፣ የገጠር መንገድ
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በሸማቾች ማህበር የሚቀርቡ ምርቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሸማቾች ተናገሩ