“በዓለ ሆሳዕና”

“በዓለ ሆሳዕና”

“ሆሳዕና” የሚለው ቃል “ሆሻዕናህ” ከሚል የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም “እባክህ አሁን አድን” ወይም “መድኃኒት” ማለት እንደሆነ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ድርሳናት የተገኘውን መረጃ ያስረዳል።

በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሐት ስለማይፈጸም ጸሎቱ የሚደረገው ከትንሳኤው በፊት በዚሁ ዕለተ ብቻ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት አባቶች ይገልፃሉ።

ኢየሱስ ክርስቶስ በበረሃ ለአርባ ቀናት በጾም ቆይቶ ካገባደደ በኋላ በሠይጣን መፈተኑና የስቅለቱ ጊዜ ሲቃረብ ወደ ኢየሩሳሌም መምጣት የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ነበር። በዚያም ወቅት ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ እንደነበርና፥ የተቀመጠባት ውርንጭላም ሰው ያልተቀመጠባትና የታሰረች ብትሆንም፣ በእርሱ ግን የእግዚአብሔር ክብር ማረፊያነት የተመረጠች እንዲትሆን አድርጎታል ብለው የእምነቱ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ዕለተ ሆሳዕና ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ በገባ ጊዜ “ሆሳዕና በአርያም፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ይሁን፤” እያሉ በማዜም የዘንባባ ዝንጣፊ እንዲሁም የለበሱትን ልብስ በመንገዱ ግራና ቀኝ እያነጠፉለትም አጅበው ተቀብለውታል። ዘንባባን ደርቆ እንደገና ህይወት የመዝራት እንዲሁም ልብስ የክብር ተምሳሌት በመሆኑ አይሁዳውያን ዘንባባ ዝንጣፊና ልብሳቸውን በማንጠፍ ለእሱ ያላቸውን ክብር በተግባር በማሳየት ጌታቸውን ተቀብሎታል ይላሉ የእምነቱ አባቶች።

ዕለቱም “ሆሳዕና በአርያም” በመባል በየዓመቱ ከትንሳኤ በፊት ባለው ሰንበት ቀደም ተብሎ ይከበራል።

በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምህሮ መሠረት በትንቢተ ዘካሪያስ 9፥9 “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በይ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” የተባለበት ዕለት ይፈጸም ዘንድ ነው።

በሆሳዕና ዕለት የእምነቱ ተከታዮች የዘንባባ ቅጠል ጭንቅላታቸውና በእጃቸው የሚያስሩ ሲሆን ምስጢሩ ጌታ ለአዳም የሰጠው ቃል ኪዳንና ከልጅ ልጁ ተወልዶ የሚያድንበትን የተስፋ ቃል ማሳያ፣ ጌታ ለድንግል ማሪያም የገባላትን ቃል ኪዳን ተምሳሌትና አዳምን ከኃጢአት ግዞት በመለኮታዊ ሀይሉ ነፃ ያወጣበት መሆኑን ነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በጌዴኦ፣ ኮሬና ቡርጂ ሀገረስብከት የይርጋጨፌ ከተማ ደብረ ምህረት ቅድስት ኪዳነ ምህረት፣ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤልና ደብረ ታቦር ቅዱስ አማኑኤል አብያተክርስቲያናት አስተዳዳሪ መላከ ሠላም ቀሲስ ድረስ ታደሰ የሚገልጹት።

ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን የኃጢአት ዕዳ ለመክፈልና ከዘላለም ሞት ለማዳን በመስቀል ላይ ተሰቅሏል። “እግዚአብሐር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” ተብሎ እንደተፃፈ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መስዋዕት የመሆን ጅማሮ ነው ይላሉ መላከ ሠላም ቀሲስ ድረስ።

ይሁን እንጂ ዝቅ ብሎ ወደ ምድር በመምጣቱ ብቻ ማንነቱን(አምላክነቱን) መቀበል ያቃታቸው ብዙዎች ነበሩ። አምላክ የሰው ልጅን ለማክበር ስጋ ለብሶ ወደ ምድር መምጣቱ ሳያንስ ለክብሩ ሌሎች መጓጓዣዎችን መጠቀም እየቻለ የአህያ ውርንጭላን መምረጡ ትሁት አምላክ መሆኑን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ድርሳት ያስነብባሉ።

አህያ በባህሪው የስክነት፤ በቀላሉ የሚያዝና የሚታዘዝ ፍጡር ተምሳሌት በመሆኑና ኢየሱስ የተዋረደውን የሰውን ልጅ በክብሩ ከፍ ለማድረግ የታሰበው የመለኮታዊ ዕቅድ ማሳያ መሆኑን የእምነቱ አባቶች ይናገራሉ።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ጌታ ሊፈፅመው ያለው ትልቅ ዓላማ ለማሳካት የሰውን ልጅ ኃጢያት በጫንቃው በመሸከም እስከሞት ድረስ መሰዋት ፍቅሩን በሚያምንና በማያምን ዓለም መካከል በመሰቀል የጥል ግድግድ ለማፍረስ የተደረገ ጉዞ ነው ዕለተ ሆሳዕና።

ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት የሰው ልጅ በኃጢያቱ ከአምላኩ ርቆ የዘላለም ሞት ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን ነገር ግን አምላክ በገባው ኪዳን መሰረት የሰው ልጅ እንደገና በምህረቱ ተጎበኘ። በዚህም በሰውና በጨለማ ሃይላት የነበረው የኃጢአት ቁርኝት በሞቱ ለዘላለም ተቋርጦ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ ተፈጠረ።

የሰው ልጆች የኃጢአት ዕዳ በጫንቃቸው ተሸክመው ከመንከራተት ውጪ መክፈል በማይችሉበት ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ዕዳ ለመክፈል በኃጢአት የቆሸሸውን የሰው ልጆች ደም፣ ኃጢአት በሌላው በኢየሱስ ደም ለማንፃት እንዲሁም ከዘላለም ሞት ለማዳን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ደሙን አፈሰሰ። በዮሐንስ ወንጌል 3፥16 እንደተባለው “እግዚአብሐር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” ተብሎ ተጽፎ እነሆ በሰሞነ ስቅለት የፍቅሩ ጮራ ከኢየሩሳሌም ወደ አለም በራ። ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን አንዲያ ልጁን አሳልፎ እስከ መስጠት የቆረጠ፣ የሰውን ልጅ መከራ የዋጀ፣ በሞቱ ህይወት ሊሰጥ አንግቦ የተሳነና በዓለም አደባባይ በተግባር የታየ የክርስቶስ ፍቅር ብቻ ነው።

መረጃዎችን ለማጠናቀር የእምነቱ ድርሳናት፣ መጽሐፍ ቅዱስና የእምነቱ አባቶች በግባትነት ተጠቅመናል፡፡ መልካም በአል!

ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን