መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ፣ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑሪዬ እንደገለፁት፤ የመድረኩ ዋና ዓላማ በገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ነዉ።
ፕሮግራሙ በሀገር ደረጃ ገጠርን መሰረት አድርጐ እየተተገበረ የሚገኝ መሆኑት የገለጹት የቢሮው ሃላፊ፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም በ8 ወረዳዎች ፕሮግራሙ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ የመንገድ ግንባታና ጥገና እንዲሁም የተንጠልጣይ ድልድይ ስራዎች የተከተቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በ8ቱም ወረዳዎች 111 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ፣ 132 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና እንዲሁም 5 የተንጠልጣይ ድልድዮች እና ዘጠኝ ልዩ ልዩ ስትራክቸሮች በፕሮግራሙ የሚከናወኑ መሆኑን ዶ/ር መሀመድ ጠቁመዋል።
ፕሮግራሙ ለክልሉ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ያሉት የቢሮው ሃላፊ፤ እስካሁን ፕሮግራሙ በተሳካ ሁኔታ እንዲሄድ እያደረጉ የሚገኙ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትን አመሰግነዋል።
በቀጣይ ጊዜም ፕሮግራሙን በልዩ ሁኔታ የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
በመድረኩ የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና (RCFSP) ፕሮግራም የ9 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እየቀረበ ሲሆን በተመረጡ አካባቢዎች ላይ የመስክ ምልከታ እንደሚደረግም ተገልጿል።
ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል