የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላምና በሀገር ግንባታ ዙሪያ ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ

ምክር ቤቱ የ2017 ዓመተ ምህረት 3ኛ መደበኛ ጉባኤና በተሻሻለው የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ዙሪያ ከአባላቱና ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደምስ ገብሬ እንዳስታወቁት፤ የጉራጌ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

ምክር ቤቱ አሁን ላይ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ መሆኑንም አስረድተዋል።

እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዞኑ ተንቀሳቅሰው በነጻነት ስራቸውን እንዲሰሩና ችግሮች ሲፈጠሩ በምክክር በመፍታት እንዲሁም የጋራ በሆኑ በሰላምና በሀገር ግንባታ ዙሪያ በጋራ በመስራት ዲሞክራሲያዊ አካሄድ የሚከተሉ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ምክር ቤቱ አስከታችኛው መዋቅር ወርዶ የተሻለ ተግባር እንዲያከናውን የመንግስት መዋቅርና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ጨምረው ገልጸዋል።

የተሻሻለው የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ በዋናነት ከፌደራል ጀምሮ በፓርቲዎች ስምምነት መጽደቁን ገልጸው፤ የስራ አስፈጻሚው የስልጣን ጊዜ ከአንድ ወደ ሁለት አመት ከፍ ተደርጎ አንድ አስፈጻሚ ለሁለት ጊዜ ብቻ እንደሚወደዳር አብራርተዋል።

የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ ክልከላዎችን ያካተተ ሲሆን ከበጀት ጋር ተያይዞም የተሻሻሉ ነገሮች መኖራቸውንና የጋራ ምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ማቋቋም ተካቶበታል።

የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፖርቲ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ እና የጋራ ምክር ቤቱ አባል አቶ ሄኖክ አብድልሰመድ፤ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የዴሞክራሲ ምህዳር ለማስፋት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

በዞኑ የዲሞክራሲ ባህል ይበልጥ እንዲጎለብት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ለውጦች የፖለቲካ ፖርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይበልጥ ማገዝ እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ምክር ቤቱ የተሻሻለውን ደንብ ተግባራዊ በማድረግና የጋራ ምክር ቤቱን በማጠናከር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ መሳተፍ እንደሚጠበቅበት አብራርተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም በተሻሻለወ መተዳደሪያ ደንብ ውይይት መደረጉ በመመሪያና በደንቡ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ እንደሚያስችላቸው ገልጸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ስራቸውን ማከናወን የሚችሉት ሰላም ሲሰፍን በመሆኑ በዞኑ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ አካል ጉዳተኞች በፖለቲካው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እድል የሰጠ መሆኑና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ አብራርተዋል።

የሚገጥሙ ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታት የጋራ ምክር ቤት ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው በመተጋገዝና በመተባበር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

በመድረኩ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አመራሮች፣ የአካል ጉዳተኞች ጽ/ቤት አመራሮች፣ የወጣት ማህበርና የክንፍ አመራሮች፣ የምክር ቤቱ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ መላኩ ንማኒ – ከወልቂጤ ጣቢያችን