የውሃ ሀብት ብክነትንም ሆነ ብክለትን ለመቆጣጠር ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንደሚገባው ተመላክቷል፡፡
የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተፋሰስ አስተዳደር ድጋፍ ለጠንካራ፣ አካታች እና ተስማሚ ለውጥ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም “ብራይት” የተሰኘውን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ የውይይት መድረክ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አብርሃ አዱኛ፤ ፕሮጀክቱ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ መጀመሩን አስታውሰው ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ትልቅ ፋይዳ ባለው ስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ወርክሾፑ ማስፈለጉን ገልፀዋል።
ኘሮጀክቱ 5 ተፋሰሶችን የያዘ ሀገራዊ ዕድገት ሊያመጣ የሚችል ነው ያሉት ዶ/ር አብርሃ፤ ባለፉት 11 ወራት በተሰሩ ጅምር ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች እየታዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀው፤ በሀገራችን ያለውን የውሃ ሀብት በአግባቡ ለማስተዳደር ፕሮጀክቱ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር፤ በውሃ ሀብት አስተዳደር ዙሪያ በክልሉ በርካታ ቅንጅታዊ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን አመላክተዋል፡፡
የውሃ ብክለትንም ሆነ ብክነትን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ህይወት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካም እየሆነ የመጣውን የውሃ ሀብት በተገቢው ማስተዳደር ያስፈልጋል ብዋል፡፡
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የሲዳማና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የግብርና፣ የውሃና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ሀላፊዎች፣ የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች የተመረጡ የዞንና ወረዳ ሀላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ: ተነሳ ተረፈ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ