የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎቱን ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ

ቢሮው ከብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት ጋር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የተሽከርካሪ ስምሪት በኢ-ቲኬቲንግ ሶፍትዌር አገልገሎት ለመስጠት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራርሟል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፓርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትልና የመሠረተ ልማት ክላስተር ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማን ኑረዲን በውል ስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ በአስር መናኸሪያዎች የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን አፈጻጸሙም የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም ትርፍ የመጫንና ከታሪፍ በላይ የማስከፈል ችግሮችን በመቅረፍ ህብረተሰቡን መታደግ ተችሏል ነው ያሉት።

ይህን ጥሩ አፈጻጸም ፈርጅ ሶስት ላይ ባሉ ከተሞች የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ ከብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት ጋር የውል ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውቀዋል።

የቢሮው ምክትልና የትራንስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሰንበቱ አባባ በበኩላቸው በክልሉ ባሉ መናኸሪያዎች የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው ይህንን መነሻ በማድረግም የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመናኸሪያዎች ላይ አገልግሎቱን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑንና ደረጃ በደረጃ በክልሉ ከተሞች ያሉ መናኸሪያዎችን የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ህብረተሰቡ ያለ ምንም እንግልትና ተጨማሪ ወጪ ሳያወጣ አገልግሎት እንዲያገኝ እንደሚያስችለው አስታውቀዋል።

በሚቀጥሉት ቀናት የውል ስምምነት በተደረገባቸው መናኸሪያዎች አገልግሎት እንደሚጀምርና መናኸሪያዎችም ለአገልግሎቱ ዝግጁ እንዲሆኑ ይሰራል ነው ያሉት።

የብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ክርስቲያን ተሾመ እንዳሉት ድርጅቱ ከዚህ በፊት በነበሩት ጊዜያት በክልሉ የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስተውሰው ዛሬ የገባው ውል በክልሉ ባሉ መናኸሪያዎች አገልግሎቱ ለማስጀመር መሆኑ አስረድተዋል።

አገልግሎቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልጸው ስራውን በሀላፊነት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አብራርተዋል።

አገልግሎቱ ተደራሽ በሚሆንባቸው መናኸሪያዎች ከክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን ወጣቶች ተመልምለው ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ ይሰራል።

ዘጋቢ ፡ መላኩ ንማኒ-ከወልቂጤ ጣቢያችን