ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተገለጸ
ከ12 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ማሰራጨቱን የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
የኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስታረቀኝ አንደባ፤ ምርታማነትን ከመጨመር ረገድ የአፈር ማዳበሪያ ወሳኝነት እንዳለውና ዘንድሮ ለበልግ እርሻ የሚውል ከ12 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶአደሮች በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የሰብል ልማት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ አሸናፊ አሳምነው በበኩላቸው፤ በዞን ደረጃ የቀረበውን የአፈር ማዳበሪያ ለወረዳዎች ማድረሳቸውንና አሁን ላይ ወረዳዎች ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ከክልል ለዞን የተላከው 7 ሺህ 2 መቶ ኩንታል ዳፕ እና 4 ሺህ 8 መቶ ኩንታል ዩሪያ በድምሩ 12 ሺህ ኩንታል መቅረቡን የገለጹት አስተባባሪው አሁን ላይ በሁሉም አካባቢዎች ስርጭት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በዞን ደረጃ እስከአሁን ከተሰራጨው ማዳበሪያ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንና ከ8 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ባንክ ገቢ መደረጉን የቡድን መሪው አብራርተዋል።
በማዳበሪያ አጠቃቀም ዙሪያ የአርሶ አደሮቹ ግንዛቤ እየጨመረ ከመምጣቱ የተነሳ አቅርቦቱም በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት አቶ አሸናፊ፤ ለዚህም የባለሙያዎች ሚና የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከአቅርቦት ውስንነት ጋር ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ከክልሉ ጋር በተያዘው አቅጣጫ መጋዘን ያለው ተሰራጭቶ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ ለማስገባት ከስምምነት መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
አርሶ አደር ጉይባ ጉንአ እና ትሩፋት ጾካደ በጎርካ ወረዳ የሱሉኮና ሻፉሌ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ ውስንነቶች ቢኖሩም የአፈር ማዳበሪያው በጊዜ እንደደረሳቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ተሾመ ፀጋዬ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለ23ኛ ዙር በተለያዩ የሙያ መስኮች በመደበኛና በማታ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 347 ተማሪዎችን አስመረቀ
በ2018 በጀት ዓመት የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል – አቶ ፍቅሬ አማን
ሚዲያን ለአዎንታዊ ነገር በመጠቀም ወጣቱ ሀገርን መገንባት አለበት – የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን