የዲላ ዩኒቨርሲቲ 14ኛው ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አካሂዷል።
የዲላ የኒቨርሲቲ የምርምር ህትመት ሥርፀት ዳይሬክቶሬት ምስጋኑ ለገሰ(ዶ/ር)፤ በዚህ ዘመን ሳይንስ ዓለምን እየገዛ ነው ብለው ዲላ ዩኒቨርሲቲም ጥናትና ምርምር ለማህበራዊ ለውጥ ጥልቀት ካለው እይታ ወደ ተግባርና ውጤት ለመቀየር የተዘጋጀ ኮንፍራንስ መሆኑን አስረድተዋል።
ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከቀረቡ 1 መቶ 87 የጥናትና ምርምር ሥራዎች መካከል በአገርና በማህበራዊ ዕድገት ላይ አጥጋቢ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው የተመረጡ 38 ምርምር ውጤቶች በኮንፍረንሱ እንደሚቀርብ አስገንዝበዋል።
የጥናትና ምርምር ሥራዎች ማህበራዊ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን የገለጹት ምስጋኑ(ዶ/ር) ከመላው ዩኒቨርሲቲዎች እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 2024 ላይ ከ4 መቶ በላይ ምርምሮችን ማሳተማቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ የጥናት ውጤቶች በተለያየ መልኩ ወደ ማህበረሰቡ በመሬት አጠቃቀም፣ በቡና፣ በእንሰት፣ በአገር በቀል ዕውቀት እና በሌሎችም በተለያዩ ቋንቋዎች እየተተረጎመ ተግባራዊ የማድረጉ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን አብራርተዋል።
በኮንፍረንሱ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥናታዊ ጹሑፍ ለማቅረብ መጥተው ያነጋገርናቸው ዶክተር ተባበር አየለ፤ የምርምር ሥራ አገርን የሚያሳድግ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሚከናወን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በአፕላይድ ሳይንስ እስፔሻላይዝድ ያደረገ ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ ሳይንስን መሠረት በማድረግ የተፈጥፎ ሀብትንና ባህልን በጠበቀ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ተዘጋጅተው የሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ወደ መሬት ወርደው የህብረተሰቡን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ምርታማነታቸውን በማሳደግ አገሪቱንና አህጉርን ከፍ የሚያደርግ ሥራ ከኮንፍራንሱ ይጠበቃል ያሉት ዶክተር ተባበር ጥናትና ምርምር ለአንድ አገር ዕድገት መሠረታዊ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ተስፋዬ ጎበና – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ከ5 መቶ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑ ተገለጸ
የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎቱን ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ
የትምህርት አጀንዳ “የሁሉም ልማት በኩር አጀንዳ ነው” ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለፁ