የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት በአሪ ዞን በኩታ ገጠም በተደራጁ አርሶ አደሮች መሬት ላይ የተዳቀለ በቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት አስጀመረ

‎የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተሻሻለ አሰራርን በመከተል በ158 ሄክታር መሬት የበቆሎና ቦሎቄ የምርጥ ዘር ብዜት እንደሚካሄድ የአሪ ዞን ግብርና መምሪያም አስታውቋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ግዛው እንደገለፁት፤ የምርጥ ዘር ብዜት ከሰብል ማምረት ባለፈ ምርምር የታከለበትና ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት በዞኑ ደቡብ አሪ ወረዳ ጨለጎድ ቀበሌ ከአካባቢ ምርታማነትና ከአርሶ አደሩን ጥንካሬና ተነሳሽነት አንፃር ሃላፊነት በመውሰድ የብዜት ስራው መጀመሩን ገልፀው በተመሳሳይ በሌሎች ዞኖችም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

‎የአሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላትና ከአርሶ አደሩ ጋር በመግባባት ከዚህ ቀደም ውጤታማ የምርጥ ዘር ብዜት መሰራቱን ገልፀው ዘንድሮም የተሻሻለ አሰራርን በመከተል በሜካናይዜሽን በታረሰ 158 ሄክታር መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

‎በተጨማሪም የግብርና ልማት ስራዎች ሁሉንም አርሶ አደሮች ያቀፈና ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ከእጅ ወደ አፍ አልፎ የኢኮኖሚ አቅም እንዲገነባ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ በመሆኑ በበልጉ የእርሻ ወቅት በዞኑ በደቡብ አሪ ባካ ዳውላና ጂንካ ከተማ አስተዳደር በበቆሎና ቦሎቄ የምርጥ ዘር ብዜት ስራው ይስራል ብለዋል።

‎የደቡብ አሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግዛው ሃይሌ በበኩላቸው፤ ግብርና ከምግብ ዋስትና ባለፈ የኢኮናሚ መሰረት ስለሆነ ከዚህ ቀደም በትንንሽ ሄክታር መሬት ላይ ይሳተፉ የነበሩ አርሶ አደሮችን በማሰባሰብ ሰፋ ባለ ሁኔታ በልቶ ከማደር ባለፈ የኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የBH 140 በቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት በወረዳው ጨለጎድ ቀበሌ ለማምረት በጋራ በመመካከር ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል፡፡

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት የዘር ብዜትና ጥራት ቁጥጥር የስራ ክፍል ሃላፊ አቶ መርነህ ታምሩ፤ በጨለጎድ ቀበሌ በ108 ሄክታር መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜቱ እንደሚከናወን ገልፀው ስራው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ከሚሰጠው የክህሎት ስልጠና ባሻገር የቅርብ ክትትል እንደሚደረግም ገልፀዋል።

‎በዘር ብዜቱ የተሳተፉት የአርሻት ልማት ማህበር ሰብሳቢ አቶ ማቲዮስ ሀዝሚ፤ ይህ የዘር ብዜት ስራን በጉጉት ሲጠብቁት እንደነበር ገልፀው ውጤታማ ስራ ለመስራት የማህበሩ አባላት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

‎በዘር ብዜት ማስጀመሪያም ፕሮግራሙ ከፌደራል የመጡ ተጋባዥ እንግዶች ሌሎች የክልል የዞንና የወረዳ የመንግስት የስራ ሃለፊዎች ባለሙያዎችና የሀይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።

‎ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን