በመርሐ-ግብሩ ላይ ከፌዴራል ጀምሮ የዞንና ከተማ አስተዳደር አመራር አካላትና የዘርፉ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን የተከናወነው የፍተሻና ሙከራ ሥራም ስኬታማ እንደነበር ተገልጿል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንደሞ እንደገለጹት፤ ይህ ኘሮጀክት በአካባቢው ሲከሰት የነበረውን የኃይል መቆራረጥ ችግር የሚፈታ በመሆኑ ድጋፍና ርብርብ በማድረግ ስኬታማ እንዲሆን ላደረጉት አካላት ምስጋና ይገባቸዋል።
አካባቢው ጥብቅ ደን ያለበት በመሆኑ ይህ የሀገር ሀብት እንዳይጎዳ በተደረገው ተጨማሪ ጥናት ጊዜ የወሰደ መሆኑን የተናገሩት አቶ አዝመራ፤ ኘሮጀክቱ ለዚህ ደረጃ መብቃቱ ለህዝቡ ትልቅ እፎይታ ይፈጥራል ብለዋል።
የፍተሻና ሙከራ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብዙ ሀብት ያለው አካባቢ ቢሆንም በመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቶ በለውጡ መንግስት በርካታ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በመከናወን ላይ ሲገኙ ከእነዚህ መካከል የመስመር ፍተሻ የተደረገው የመቱ ማሻ ባለ 230 ቦልት ሳብስቴንሽን ግንባታ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
ለጋራ ህዝቦች ተጠቃሚነት የኢሉባቦር ዞንና የሸካ ዞን በጋራ የጀመሩት የመተባበር ስራ በመብራትና በአስፓልት መንገድ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ለዚህ ሁሉ ስኬት ላበቁት ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ምክትል ስራ አስፈፃሚ አንዱአለም ስዓ እንደገለጹት፤ ኘሮጀክቱ ለህብረተሰቡ የኃይል መቆራረጥ ችግርን በመቅረፍ ረገድ ትልቅ አቅም ያለውና በዘመናዊ መሳሪያዎች የተደራጀ ነው።
ከመቱ-ማሻ በወፍ በረር 70 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው174 ከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር “የኮንዳክተር” ዝርጋታ መከናወኑንም የመቱ-ማሻ መስመር ዝርጋታ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው አሳዬ ተናግረዋል።
ስራው አድካሚና የተፈጥሮ ጫናን በመቋቋም መከናወኑን ተናግረው፤ የኘሮጀክቱ ለዚህ ደረጃ መብቃት የአካባቢው ህዝብና ባለድርሻ አካላት ትብብር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ኘሮጀክቱን በ18 ወራት ለማጠናቀቅ ውል የተገባ ቢሆንም ከዓለም ባንክ አሰራር ጋር ለማስታረቅ ተጨማሪ ጥናት በማስፈለጉ ይጠናቀቃል በተባለው ጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ 5 ዓመት በላይ መውሰዱም በዚሁ ወቅት ተመላክቷል።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው እያንዳንዳቸው 31 ነጥብ 5 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎመሮች እንዲሁም አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢና ስድስት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት።
በመርሃ ግበሩ ላይ የተገኙት የማሻ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው የሀይል ማከፋፈያ ተጠናቆ ዛሬ በሙከራ ደረጃ ላይ በመድረሱ መደሰታቸውን ገልፀው ይህም ከዚህ በፊት በከተማ የሚታየውን የመብራት መቆራረጥ ከመቅረፍ በተጨማሪ በደን ሀብት ላይ የሚደርሰውን ውድመት የሚያስቀር ነው ብለዋል።
አሁንም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት እንዲችል አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ነዋሪዎቹ ከተማዋ ከሌሎች ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንዲትሆን የተጀመሩ ልማቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እናስቀጥላለን ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት በከተማው የነበረውን የመብራት መቆራረጥ ችግር ለመቅረፍ የለውጡ መንግስት ስላከናወነው ተግባር ምስጋና አቅርበው፤ የዚህ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ወጣቶች ስራ ፈጣሪ በመሆን እንዲሁም በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ለሀገር የሚጠቅም ተግባር እንዲፈፅሙ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ከፌደራል ጀምረው እስከታች ያሉት የመብራት ሀይል ባለሙያዎች እንደገለፁት ከብዙ አመታት ልፋት በኋላ በዚህ ደረጃ ላይ በማድረሳቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ ካሳሁን ደንበሎ – ከማሻ ጣቢያችን
More Stories
በሀገሪቷ ባለፉት 7 የለዉጥ አመታት የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለፁ
ድልና ውጤት የሚመጣው በምኞት ሳይሆን ጠንክሮ በጋራ መሥራት ሲቻል ነው ሲሉ ዶ/ር መሪሁን ፍቅሩ ተናገሩ
መጋቢት 24 በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ የፖለቲካ እጥፋት የተደረገበት ነው – ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ