ባለፋት 7 አመታት በለውጡ ስርዓት የተመዘገቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትሩፋቶች ዙሪያ በሚዛን አማን ከተማ ውይይት ተካሄደ

በውይይቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚዛን አማን ከተማ የብልፅግና ህብረት አባላት ተሳትፈዋል።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የተደረገበት መሆኑ በዚሁ ወቅት ተመላክቷል።

በህዝብ ጠያቂነት በመጣው ለውጥ የህዝብን ፍላጎትና ጥያቄ የሚመልስ የሀገር አንድነትን የሚያስጠብቅ ስርዓት የተጀመረበት መሆኑን በክልሉ የሚዛን ክላስተር ብልፅግና ህብረት ሰብሳቢ አቶ ፀደቀ ከፍታው ገልፀዋል።

ለህብረቱ አባላት በቀረበው የመወያያ ሰነድ ላይ ባለፉት 7 አመታት በፖለቲካ ዘርፍ ሁሉም ዜጎች እኩል ለሀገር ልማትና እድገት የድርሻውን እንዲወጡ ሚያስችል የፖለቲካ ምህዳር የተፈጠረበት መሆኑ ተገልጿል።

ለውጡ ቀድሞ የተሰሩ ስራዎችን በሙሉ አጥፍቶ ከአዲስ ከመጀመር ይልቅ ጠንካራ ጎኖችን በማጠናከር ሊስተካከሉ በሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ ለውጥ በማድረግ ሀገር የማዳን ስራ መሰራቱን የህብረቱ ሰብሳቢ አቶ ፀደቀ ከፍታው ገልፀዋል።

በኢኮኖሚ ዘርፍም ከተመፅዋችነት ወደ ለጋሽነት መሸጋገር እንደሚቻል የሚያሳዩ በርካታ ስራዎች በግብርናው፣ በኢንዱስትሪውና ሌሎች ዘርፎች የተሰሩበት መሆናቸውና እነዚህንም አጠናክሮ በማስቀጠል በተለይም የልማት ኢንሼቲቮችን ፈጥኖ ወደ ተግባር ከመግባት አንፃር የተፈጠሩ ልዩነቶችን በመቅረፍ ወጥ በሆነ መልኩ ሁሉም አካባቢዎች በእኩል ፍጥነት መልማት እንዲችሉ መስራት እንደሚገባም በውይይቱ ተገልጿል።

በሌላ በኩል በዲፕሎማሲው መስክ የተገኙ ውጤቶች ቀጠናዊና አለማቀፋዊ ሁኔታዎችን የተረዳና የሀገርን ጥቅም ያስቀደሙ ስራዎች መሰራታቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ከመከሩባቸው ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው።

በፍትህና ፀጥታ ተቋማት ላይ የተከናወኑ ተግባራትም ባለፉት 7 አመታት አመርቂ ውጤት ከተመዘገበባቸው ዘርፎች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን የህብረቱ አባላት ውይይት አድርገውበታል።

ከዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ አንፃር የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን በማስቀረት ተቋማቱ በተቋቋሙበት ህግና ስርአት እንዲመሩ መሰረት ተጥሎ ወደ ተግባር መገባቱም በቀጣይ ለሚኖረው የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ መሰረት የተጣለበት መሆኑ በውይይቱ ተገልጿል።

ከመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም የመጣው የስርዓት ለውጥ በኢትዮጵያ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከመመለስ አንፃር በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልም የዚሁ ውጤት መሆኑ በውይይቱ ተገልጿል።

“የመጋቢታውያን ፍሬዎችና የነገ ተስፋዎች” በሚል መሪ ቃል በተደረገው ውይይት ላይ የተገኙ ለውጦችን በሪፎርም በማፅናት ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የህብረቱ አባላትና ደጋፊዎች የድርሻቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።

ዘጋቢ፡ ነብዩ መካሻ – ከሚዛን ጣቢያችን