ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ፆም ወቅት ያሳየውን የመረዳዳትና የመተሳሰብ ልምዱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠየቀ

ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ፆም ወቅት ያሳየውን የመረዳዳትና የመተሳሰብ ልምዱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠየቀ

‎በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው 1ሺህ 446ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል በኣሪ ዞን ጂንካ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

‎1ሺህ 446ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል ላይ የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ የጂንካ ከተማ ከንቲባና ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ህዝበ ሙስሊሙ ተገኝተዋል።

‎የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ እንደገለፁት፤ ማህበረሰብ ሰላም እንዲጠበቅ አንድነት እንዲጎለብት አብሮ በመረዳዳት የሚሰራው ስራ ለሌላው አርአያ ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ በእንዲህ አይነት መልክ አምራችሁ ተውባችሁ በአንድነት በአሉን ስታከብሩ ፈጣሪ ይሰማናል ያሉት ‎የጂንካ ከተማ ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሺ፤ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በጋራ በዓሉን ሲያከብሩና በችግርም በደስታም ለሰላሙም ሆነ ለልማቱ በጋራ ሲውሉ ደስ እንደሚል ነው የገለጹት።

‎የኣሪ ዞን እስልምና ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ጀማል መሀመድ በበኩላቸው፤ የዘንድሮውን የረመዳን በዓል ከወትሮው ለየት የሚያደርገው በሁሉም የከተማውና የዞኑ አካባቢዎች በሚገኙ መስጊዶች በሰላማዊ ሁኔታ እርስ በእርስ በመተባበርና በመተሳሰብ በጥሩ ሁኔታ ማሳለፋቸው እንደሆነ ገልፀው ህዝበ ሙስሊሙ በአሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

‎የእምነቱ ተከታዮች በሰጡት አስተያየት፤ የረመዳንን ፆም በየመስጊዱ አላህን በመገዛትና በመታዘዝ በፀሎት በሶላትና በሰደቃ እርስ በእርስ በመረዳዳትና በመተጋገዝ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ጊዜያት በተለየ መልኩ የረመዳን ፆምን እንዳሳለፉ ገልፀዋል።

‎ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን