ሙስሊሙ ማህበረሰብ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር በታላቁ የረመዳን ወር አብዝቶ ሲሰራቸው የነበሩ መልካም ስራዎቹን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት የዕምነቱ መሪዎች አሳሰቡ

ሙስሊሙ ማህበረሰብ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር በታላቁ የረመዳን ወር አብዝቶ ሲሰራቸው የነበሩ መልካም ስራዎቹን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት የዕምነቱ መሪዎች አሳሰቡ

1ሺ 446ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሚዛን አማን ከተማ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡

በእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ በዓላት መካከል የኢድ አልፈጥር በዓል አንዱ ነው።

በዓሉ የታላቁ የረመዳን ወር መጠናቀቅን ተከትሎ የሚከበር ሲሆን የሀይማኖቱ ተከታዮች በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስርአቶች ያከብሩታል።

የዘንድሮው 1446ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከብሯል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸይኸ አደም መሐመድ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1ሺ 446ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከበር በረመዳን የጾም ወቅት የነበረውን መረዳዳት እና አብሮነት ይበልጥ አጠናክረን በማስቀጠል ሊሆን እንደሚገባው ሸይኸ አደም ተናግረዋል፡፡

በተለይ የረመዳን ወር ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንደነበር ገልፀው ለዚህም የፀጥታ አካላት ላደረጉት ተሳታፎ ምስጋና አቅርበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ እስልምና ጉዳዮች ምክር ሰብሳቢ መምህር መሀመድ ሰይድ እንኳን ለ1446ኛው የኢድአልፈጥር በዓል በሠላም አደረሳችሁ ብለው ፆሙ የሰው ልጅ ወደፈጣሪው እንዲመለስ የሚያደርግ ታላቅ ወር ነው ብለዋል።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም እንደተናገሩት፤ በዓሉ ሲከበር የሰዎች ጥሩ ስብዕና የሚታይበትና የተቸገሩ ወገኖችን የመርዳት እና የመንከባከብ ባህልን ይበልጥ በማስቀጠል ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ሙስሊሙ ማህበረሰብ ይህንን ታላቅ በዓል ሲያከብርም በከተማዋ የተጀመሩ የሠላም የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በቅርበት በመከታተልና በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በበዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይና የአስተዳደር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ እሸቱ ሻንበል እንደተናገሩት፤ የዞኑ ሙስሊሞች በቅዱሱ የረመዳን ወር ሲያሳዩ የበረውን የሠላም፣ የመደጋገፍና የአንድነት እሴት ይበልጥ ማስቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል

በበዓሉ ያነጋገርናቸው የዕምነቱ ተከታዮች የረመዳን ወር መልካም ስራዎች በመስራት ማሳለፋቸውን ተናግረው ይህንን በጎ ተግባር በቀጣዮቹ ጊዜያትም ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን