በልዩ ወረዳዉ በመጋቢት ወር የተገኙ ትላልቅ ድሎችን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ

 በልዩ ወረዳዉ የመጋቢታዊያን ቀን በማስመልክት “ትላንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ከተማ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተደረገ።

በዚህ ወቅት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ምስጋናዉ ማትዮስ እንደገለፁት በአገር አቀፍ ደረጃ በመጋቢት ወር በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

በተለይም የህብረተሰቡን ልማታዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ስራ ላይ የዋሉበት ወር መሆኑንም ገልፀዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በበኩላቸዉ መጋቢት ወር የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር ደ/ር ዐቢይ አሕመድ  ወደ ስልጣን የመጡበትና በአገር አቀፍ ብሎም በልዩ ወረዳው የህብረተሰቡ የመልማት ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት ወር መሆኑንም ገልፀዋል።

ይህንን በማስቀጠል ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ  እንደሚገባም አክለዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ አቡበክር ዱላ የመጋቢት ወር ድሎችን ማስቀጠል እንደሚገባና በተለይም ወጣቱ ትዉልድ አብሮነትንና የአከባቢዉን ሰላም ማስጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል።

የልዩ ወረዳዉ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ጁሃር ጀማል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የህብረተሰቡን በተለይ የወጣቱን ጤና ሰላም እና አንድነት ለማስጠበቅ ያለዉ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ  ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ፕሮግራሙ ወጣቶች ራሳቸውን ከሱስ በመጠበቅ ጤናማና ንቁ እንዲሆኑ የሚያስችላው ከመሆኑም በሻገር እርስ በራሳቸው ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩና ለአካባቢያቸውና ለሀገራቸው ሰላም መጠበቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያግዛቸው  መሆኑን የፕሮግራሙ ተሳታፊ ወጣቶች ተናግረዋል ፡፡

በመሆኑም መሰል የጋራ ስፖርት ፕሮግራሞች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልፀዋል ፡፡

በአካል ብቃት እንቅስቃሴዉ የክልሉ የስራ ሀላፊዎች፣ የልዩ ወረዳዉ አመራሮች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ ፡በሪያድ ሙህዲን-ከወልቂጤ ጣቢያችን