የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከክልሉ ንግድ ዘርፍ ምክር ቤት ጋር የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረኮችን ለማካሄድ የሚያስችል የግብ ስምምነት ተፈራረሙ

‎‎

‎ስምምነቱ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ያላቸውን ቁርኝት እንደሚያጠናክር ተመላክቷል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን እንገለፁት፤ የግብ ስምምነቱ በዋናነት የምክክር መድረኮችን ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመፍጠር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የአሰራር ማቀፍ በማስፈለጉ ነው።

‎የግሉ ዘርፍ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የላቀ አበርክቶ እንዲኖረው አቅዶ እየሰራ በመሆኑ ዘርፉ በየደረጃው በምክር ቤት ተደራጅቶ የሚንቀሳቀስበትና ለላቀ ውጤት የሚበቃበት አካሄድ እየተሰራ ነው ብለዋል።

‎ክልሉ ባለ ብዙ ፀጋ ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ይህንን ፀጋ ለሚመለከታቸው አካላት አጉልቶ በማሳየት ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ አልሚዎች የማስተዋወቅና ኢንቨስተሮችን ወደ ክልላችን የመጋበዝ ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ቢታኔ በበኩላቸው፤ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የጋራ ምክክር የሚያደርግበትና በሁሉም መዋቅሮች ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት የግብ ስምምነት እንደተፈራረሙ አስረድተዋል።

‎ንግድና ኢንቨስትመትን ማሳለጥ ዋና አላማው ያደረገው ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቱ ሀገሪቱ የምትፈልገውን ልማት ለማሳካት የሚያስችል መሰረት መሆኑን አስታውቀዋል አቶ ቦጋለ።

‎በመንግስትና በንግዱ ዘርፍ እንደ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ መንግስት ከንግዱ ማህበረሰብ የሚፈልገውን መረጃ በመውሰድ ችግሮችን እንዲፈቱ በማድረግና ሁሉም ነጋዴ ሰላማዊ የሆነ የንግድ ስርአት እንዲኖር ማስቻል ነው ብለዋል።

‎በክልሉ ከ1መቶ 48ሺ በላይ ነጋዴዎች መኖራቸውን ገልፀው ሁሉም ነጋዴ ወደ ተቋሙ በመምጣት ችግሮችን በጋራ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

‎ዘጋቢ፡ ገነት መኮንን – ከአርባምንጭ ጣቢያችን