በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ በአቶ ሳሙኤል ዳርጌ መሪነት የመስክ ምልከታ እያደረገ የሚገኘው የሴክተሩ አመራሮች ቡድን በከምባታ ዞን አድሎ ዙሪያ ወረዳ ሆለገባ ቀበሌ የሆለገባ ጤና ኬላ የስራ እንቅስቃሴን እየጎበኘ ነው

ከምልከታው ጎን ለጎን በከምባታ ዞን አድሎ ዙሪያ ወረዳ ሆለገባ ሁሉአቀፍ ጤና ጣቢያ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌና የከምባታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሄራሞ የግንባታውን የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የክልሉን ህዝብ በጤናው ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ የጤና ፕሮግራሞችን ለመተግበር ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም አጠቃላይ ጤና ኬላዎችን የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ ግንባታዎቹ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚተገበሩ መሆናቸውን በመግለጽ ክልሉም ካለው ሀብት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የሆለገባ ጤና ኬላ ከወረዳው ባለፈ በአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያገለግል በመሆኑ መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና አገልግሎት መስጠት እንዲችል በተገቢው መደራጀት እንዳለበት አሳስበዋል።

የሚመደቡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ከተወጡና መከላከልን መሠረት ያደረጉ የጤና ተግባራት ላይ በትኩረት ከተሰራ የህብረተሰቡን ጤና ማረጋገጥ እንደሚቻልም አቶ ሳሙኤል አስገንዝበዋል።

የከምባታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሄራሞ በበበኩላቸው፤ ጤናማና አምራች ማህበረሰብን ለመፍጠር የጤና አገልግሎት ሽፋን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና አገልግሎት መስጠት ለህክምና የሚወጣውን ወጪ የሚቀንስ በመሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።

ለዚህም ጤና ኬላውን ወደ ሁሉ አቀፍ ጤና ኬላ ለማስፋፋት መታሰቡ አጋዥ እንደሆነ አንስተዋል።

በከምባታ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ጆሬ ሁሉ አቀፍ ጤና ኬላ የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ የተደረገ ሲሆን በቀጣይም ወደሌሎች አካባቢዎች የጉብኘቱ ስራ የሚቀጥል ይሆናል።

ቡድኑ በጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ፣ በስልጤ ዞን ምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ እና በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ የፅዱ መንደር ትግበራና የጤና ተቋማት የስራ እንቅስቃሴ ሰሞኑን ምልከታ ማድረጉ ይታወሳል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን