የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ የግብርና ልማት አካላት ግንኙነት አማካሪ ካውንስል መድረክ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ተካሂዷል።
የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘነበ አብርሃም፤ የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በዞኑ ግብርና በርካታ ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
መድረኩን የመሩት የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታጠቅ ዶሪ እንደገለጹት፤ በቅንጅትና በተሳትፎ የተሰሩትን ሥራዎች ለማስቀጠል የሚገጥሙ ማነቆዎችን እየፈቱ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።
“ከዚህ በፊት ዘር ሰጥተን የደገፍናቸው አርሶ አደሮች በምግብ ዋስትና እራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ የሠራንበት አግባብ በቂ እንዳልነበረ አውቆ መሥራት” ከሁሉም ባለድርሻ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን አሳስበዋል።
የግብርና ምርምር ተቋማትም የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና ምርታማነትን ለመጨመር በሚሠሩ ሥራዎች ላይ በትጋት እየተሳተፉ በዕውቀት መደገፍ የሚጠበቅ ተግባር ቢሆንም በዚህ ልክ አለመሠራቱን አንስተው፤ በቀጣይ ጠንካራ ቅንጅት ያስፈልጋል ብለዋል።
የኤፍ ሲ አር ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ታምራት ተሰማ፤ የምግብ ሥርዓትን ለማጠናከር በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ፈተናዎችን እያረሙ ለመሄድ መድረኩ ወሳኝ መሆኑን ተናግረው፤ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የባህር ዛፎችን እያነሱ በሌሎች ሰብሎች የመተካት ሥራና በቀበሌ ላይ ያሉ የአርሶ አደሮችን ማሰልጠኛ ማዕከላትን ሞዴል በሆነ መንገድ ሰብሎችን እያመረቱ ለሌሎች ማስተማሪያ ሊሆን በሚችል መልኩ መስራት እንደሚገባ ተገልጿል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በግብርና ሥራዎች አፈጻጸም ላይ የነበሩ ችግሮችን ገምግመው ለማሳለጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ ተስፋዬ ጎበና – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የማህበረሰቡን አንድነት፣ ሠላምና ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
በክህሎት ፣ በቴክኖሎጂና በተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውድድር ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ
በሀገሪቷ ባለፉት 7 የለዉጥ አመታት የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለፁ