የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያጠናክሩ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የገደብ ወረዳ አስተዳደር ገለጸ

የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያጠናክሩ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የገደብ ወረዳ አስተዳደር ገለጸ

ወረዳውን ከአጎራባች ወረዳዎችና አዋሳኝ ክልል ጋር የሚያገናኝ የመንገድ ጥገና ሥራ በተጀመረበት ወቅት የገደብ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ምትኩ እንደገለጹት በወረዳው በሚገኙ 13 ቀበሌያት የመንገድ ችግር መኖሩን ጠቅሰው ይሄን ለመቅረፍም እየተሰራ ነው፡፡

የተጀመረው የመንገድ ጥገና ሐርሙፎ-ሺፎ ኮቾሬ ወረዳን ከወረዳው ጋር ከማገናኘት ባለፈ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያጠናክራል ያሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፣ አርሶአደሩ ያመረተውን ምርት  ወደ ገበያ ለማውጣትና  ወደ ህክምና ተቋም ለመሄድ የነበረውን ችግር እንደሚቀርፍ ተናግረዋል።

መንገዱ ከፍተኛ ችግር የነበረበት ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በገደብ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሽፈራው ወረዳውን ከአጎራባች ወረዳዎችና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቀበሌዎች ጋር  የሚያገናኙ መንገዶች በወረዳው ከሚሠሩት ባለፈ፣ ከገደብ ሐርሙፎ-ሺፎ ኮቾሬ ወረዳን የሚያገናኝ 17 ኪ.ሜ የጥገና መንገድ ማስጀመራቸውን ተናግረዋል።

ለበርካታ ጊዜያት የመንገድ ጥገናው እንዲደረግላቸው ሲጠይቁ ከነበሩት የአከባቢው ነዋሪዎችም መንገዱ መሠራቱ ወደ ህክምና ተቋማት ለመሄድና የንግድ ሥራ እንቅስቃሴን ያለችግር ለማከናወን እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ውብሸት ካሣሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን