በጤና ጣቢያው ፈጣንና ቀልጣፍ አገልግሎትን በመስጠት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የሸኮ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
በጤና ጣቢያው በካርድ ክፍልና በዕለታዊ ገንዘብ መቀበያ አካባቢ የሚታዩ ጫናዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት እየፈጠረ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት እንዲፈቱላቸው የሸኮ ጤና ጣቢያ ተገልጋዮች ጠይቀዋል።
የሸኮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታምራት ምናሴ በሸኮ ጤና ጣቢያ ለህብረተሰቡ እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት እየጎበኙ ባለበት ወቅት ለደቡብ ሬዲዮና ቴለቪዥን ድርጅት ሚዛን ቅርንጫፍ ጣቢያ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፤ አምራች ዜጋን ለመፍጠር የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ከምንም በላይ ወሳኝ ነው።
በከተማ አስተዳደሩ የጤና መድህን አባልነት ክፍያን ከመቶ በላይ የፈፀሙት የህብረተሰብ ክፍሎች የተሻለ አገልግሎት አግኝተው የጤና ችግራቸው እንዲፈታላቸው እየተደረገ ባለው ጥረት የአገልግሎት አሰጣጥን በሚመለከት ቀንና ማታን ጨምሮ በሳምንት 4 ጊዜ ጉብኝት እያደረጉ እንደሚገኙ ከንቲባው ተናግረዋል።
በጤና ጣቢያው ፈጣንና ቀልጣፍ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ በመስጠት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሸኮ ወረዳ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን በየጊዜው የህዝብ ውይይትን በማድረግ ችግሮቹ እንዲፈቱ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ታምራት ገልፀዋል።
በሸኮ ጤና ጣቢያ ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረውን የመድኃኒት ዕጥረትን ለመቅረፍ በየሩብ ዓመቱ ከ350 እስከ 400 ሺህ ብር በላይ በጀት መድበው ግዥ እየፈፀሙ መሆናቸውን ከንቲባው አብራርተዋል፡፡
በተለይም ነፍሰ ጡር እናቶች ለተሻለ ህክምና ወደ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ቲችንግ ሆስፒታል የሚሄዱትን ችግሮች ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ ከሸኮ ወረዳ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን የCBC ማሽን ግዥ መፈፀሙንም አቶ ታምራት ተናግረዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ቦታ ለማድረስ በካርድ ክፍል፣ በዕለታዊ የገንዘብ መቀበያ እንዲሁም የጤና መድህን አባል መመዝገቢያ አካባቢ የሚስተዋሉትን ዕጥረቶች የሰው ሀይልን በመጨመር እንደሚፈታም ከንቲባው አሰረድተዋል።
ተገለጋዮቹን በቀይ፣ በቢጫና በአረንጓዴ በመለየት እንደየህመማቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚታከሙበትን ሁኔታ በመፍጠር በትኩረት ይሰራል ያሉት አቶ ታምራት፤ የመድኃኒት አቅርቦት ዕጥረትን ለመቅረፍ በቀጣይ የማህበረሰብ መድኃኒት መድብር ለመክፈት መታቀዱንም ገልፀዋል።
የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የጤና መድህን አባል በመሆን የጤና አገልግሎትን እንዲያገኝ እየተሰራ እንደሚገኝ በከተማ አስተዳደሩ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ከድር ይማም ተናግረዋል።
ሁሉም ማህበረሰብ “ጤናዬ ለራሴ ነው” በሚል መሪ ቃል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አስተባባሪው አውስተው፤ በጤና ጣቢያው ይነሳ የነበርውን የመድኃኒት ዕጥረት ለመፍታት የሸኮ ከተማ አስተዳደር በወሰደው ቁርጠኛ አቋም ከስር ከስር ግዥ ተፈፅመው ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የማደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በከተማና በወረዳው በ17 ቀበሌዎች የሚገኙ 39 ሺህ 979 ሰዎችን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝ የሸኮ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ካሳ ገልፀው፤ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆን የመድኃኒት ችግር እየተቀረፈ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከተመሰረተ 7 ወራት ውስጥ የሸኮ ከተማ አስተዳደር ለጤና ጣቢያው በሰጠው ትኩረት የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የባለሙያ ስነ-ምግባርና የጥቅማ ጥቅም ጉዳዮች ተፈተው ባለሙያዎች በተነሳሽነት እየሰሩ እንደሚገኙም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በየቀኑ ከ200 እስከ 300 ሰዎች በጤና ጣቢያው የሚስተናገዱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በካርድ ቤትና በገንዘብ መቀበያ አካባቢዎች የሚታዩ ጫናዎችን ለመቀነስ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ሰለሞን አውስተው፤ ከግቢ ማሳጠር ጀምሮ ከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን ድጋፍ ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
ካነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች መካከል ወይዘሮ አየለች አምቦና አቶ ተሾመ ሺበሺ ከሸኮ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም አቶ ካሳሁን ዶርማዬና አቶ መኮንን ውቤ ከሸኮ ወረዳ እንደገለፁት፤ የተሻለ አገልግሎት በጤና ጣቢያው እያገኙ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ወደ ጤና ጣቢያው ሲመጡ የመድኃኒት ዕጥረትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንደነበረ አስተያየት ሰጪዎች ገልፀው፤ በአሁን ሰዓት ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ለህክምና አምጥተው ተገቢውን አገለግሎት ያገኙ ቢሆንም በካርድ ክፍልና በገንዘብ መቀበያ አካባቢ የሚታዩ ጫናዎችን የሚመለከታቸው አካላት እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የማህበረሰቡን አንድነት፣ ሠላምና ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
በክህሎት ፣ በቴክኖሎጂና በተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውድድር ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ
በሀገሪቷ ባለፉት 7 የለዉጥ አመታት የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለፁ