በ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች በክልልና ሀገር አቀፍ ምዘናዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ገለፀ
ከልዩ ወረዳው መምህራን ከሚሰጡ የማጠናከሪያ ትምህርቶች ባሻገር ከሆሳዕና መምህራን ኮሌጅና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለተማሪዎች እገዛ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ሀሰን እንደገለፁት፤ በትምህርት ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መለኪያ ተማሪዎች በክልላዊና ብሔራዊ ምዘናዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት ነው፡፡
በመሆኑም ባለፉት አመታት አጋጥመው የነበሩ የትምህርት ስብራቶችን በጥናት በመለየት በልዩ ወረዳው የትምህርት ቤቶች አመራር ሪፎርም በማድረግ የተሻለ እውቀትና ልምድ ያላቸው መምህራን የመመደብ፣ የትምህርት ግብዓት የማሟላት፣ የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠትና ሌሎችም ተግባራት በማከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በየትምህርት ቤቶቹ በመደበኛነት ከሚሰጡት የማጠናከሪያ ትምህርቶች በተጨማሪ ከሆሳዕና መምህራን ኮሌጅና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለተማሪዎች እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ አህመድ አስታውቀዋል።
ከሶስት ነጥብ አምስት ሚልየን ብር በላይ በመንግስትና በህበረተሰቡ ተሳትፎ ገንዘብ በመሰብሰብ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተዘጋጁ መፅሐፍትን የማሳተምና ለትምህርት ቤቶች የማሰራጨት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ሶስት ነጥብ ሶስት ሚልየን ብር በማሰባሰብና በማሳተም ቀሪ መፀሐፍትን ተደራሽ ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝም ሃላፊው አብራርተዋል፡፡
በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች በተለይም በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት አይነቶች የመምህራን እጥረት መኖሩንና ቅጥር ለመፈፀም በተደጋጋሚ ማስታወቂያ ቢወጣም ገቢያ ላይ በሚፈለገው ልክ ማግኘት አለመቻሉን አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል የሚቻለው ከተማሪዎች ከራሳቸው ጀምሮ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ሲታከልበት መሆኑንም ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
አብድረሂም በደዊ በልዩ ወረዳው የወማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሲሆኑ ፋሪስ ሀሰን የፈቃዶ አንደኛና መካከለኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ናቸው፡፡
በትምህርት ቤቶቹ ክልል አቀፍና ብሔራዊ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርቶች በተለየ መልኩ አየተሰጠ ከመሆኑም ባሻገር ከሆሳዕና መምህራን ኮሌጅና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለተማሪዎች እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ተማሪዎች ሳይዘናጉ በስነ ልቦናና በክህሎት ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡን ተማሪዎችም ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
በቀጣይ ከመምህራንና ከመፅሐፍት እጥረት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የማህበረሰቡን አንድነት፣ ሠላምና ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
በክህሎት ፣ በቴክኖሎጂና በተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውድድር ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ
በሀገሪቷ ባለፉት 7 የለዉጥ አመታት የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለፁ