ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 13 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ በጋሞ ዞን የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት አስታወቀ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በሚደረገው ሂደት 13 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ በጋሞ ዞን የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫውን ከአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ተረክቧል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ለአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ባስረከቡበት ወቅት የአርባምንጭ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ ሊዲያ ካንቲባ እንደተናገሩት፤ በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገርን አጽንተው እንዳቆዩ አርበኛ አያቶቻችን ዛሬም ትውልዱ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ አሻራውን በማሳረፍ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ እያደረገ ይገኛል።
አክለውም የቀደመ ማንነታችንን በማሳየት ብሔራዊ ኩራታችን የሆነው ግድባችን እንዲጠናቀቅ ሌት ከቀን በመረባረባችንና በመተጋገዛችን ለገጠመን ጠላታችን ሳንበገር የሀገር ክብር የሆነውን ማሳየት ችለናል ነው ያሉት።
የአርባምንጭ ዙርያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ዘይቴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከውጭ ጫና ተላቆ የግንባታ ሂደቱ 97 በመቶ በመድረሱ ታላቅ ኩራት ይሰማናል።
እንደ ከዚህ ቀደም የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር በስጦታ፣ በቦንድ ግዢና በዓይነት አሁን የተሰጠውን 13 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ገቢ የማሳባሰቡ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በደማቅ አቀባበል የኢትዮጵያ ህዳሴ ዋንጫ የተረከበው የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት የተሰጠውን ኮታ በአግባቡ በመፈጸም ለምዕራብ ዓባያ ወረዳ ለማስረከብ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
ከአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ያነጋገርናቸው በሰጡን አስተያየት ከዚህ ቀደም በስጦታ፣ በቦንድ ግዥና በዓይነት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው አሁንም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ሰለሞን አላሶ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በሁሉም ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሴቶች የልማት ህብረትንና የስትሪንግ ኮሚቴ እንቅስቃሴን ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
የሴቶች የልማት ህብረትን በማጠናከር የሴቶችን ተጠቃሚነት በይበልጥ ማረጋገጥ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
በዞኑ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ የጋሞ ዞን አሰተዳደር አሰታወቀ