የበጋ መስኖ ስንዴ ስራዎች እና የሩዝ ምርትና ምርታማነትን የመጨመር ጅምር ተግባራት ውጤታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለጸ

የበጋ መስኖ ስንዴ ስራዎች እና የሩዝ ምርትና ምርታማነትን የመጨመር ጅምር ተግባራት ውጤታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተጀመሩ የበጋ መስኖ ስንዴ ስራዎች እና የሩዝ ምርትና ምርታማነትን የመጨመር ጀምር ተግባራት ውጤታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ ተግባሩን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ የሸካ ዞን አስተዳደር ገለጸ፡፡

የሸካ ዞን ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛ ዙር 11ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 22ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የበጀት አመቱ የግማሽ አመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በማድመጥ ቀጣይ የስራ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ምክር ቤቱ ባካሄደው ጉባኤ የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት ከአስፈጻሚ አካላት ሪፖርት መነሻ ከምክር ቤቱ አባላት በተነሳው አስተያየትና ጥያቄ ዙሪያ በሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪና በአስፈፃሚ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የቀረበውን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት መነሻ በማድረግ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት በወቅቱ ያለመጠናቀቅ እና የመብራት መቆራረጥ ችግሮች መቀረፍ እንዳለባቸው በምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል።

የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ምቹ ማድረግ ላይ የተጀመሩ አንቅስቃሴዎች መጠናከር እንዳለባቸው፣ በግብርና ዘርፍ እንዲሁም የኩታ ገጠም እርሻ ላይ የተጀመሩ ስራዎች በማስቀጠል የእንሰት፣ ቡናና የጓሮ አትክልት ላይ ውጤታማ ለውጥ ማስመዝገብ ላይ መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ህገ-ወጥ የቡና ግብይት ማስቆም ላይ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት የገለፁት አባላቱ፤ በድንበር አካባቢ የሚታዩ የጸጥታ ችግር ተከታታይነት ያለው ውይይት በማድረግ እልባት እንዲሰጥ፣ በፍትህ ዘርፍ አልፎ አልፎ የሚሰሩ አግባብነት የሌላቸው አሰራሮች መፈተሽ እንዳለባቸው እንዲሁም በእግዚቢትነት የተያዙ ንብረቶችን በህግ አግባብ ከማስተናገድ አኳያ ትኩረት ቢደረግ የሚሉት ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ፤ የተጀመሩ የበጋ መስኖ ስንዴ ስራዎች እና የሩዝ ምርትና ምርታማነትን መጨመር ተግባራት ጅምር ስራዎች ውጤታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ ተግባሩን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብና በማስተዳደር በበጀት ዓመቱ ውጤታማ ሥራ በመስራት በገቢ አሰባሰብ ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚደረግና የአስፈፃሚ አካላት ቅንጅት እንደሚያስፈልግ የገለፁት አቶ አበበ፤ የማሻ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ አፈፃፀም የተሻለ መሆኑንና ከማስፋፊያ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።

በዞኑ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት ጅምር ስራዎች የተሻሉ ቢሆንም ከህዝብ ፍላጎት አንፃር አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተተገበሩ ያሉ ስራዎችን በማጠናከር የተመረተውን ምርት አሟጦ ለማዕከላዊ ገበያ የማቅረቡ ስራ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ጠቁመዋል።

በዞኑ የተጀመሩ የተማሪ ምገባ ፕሮግራም የተሻለ ዉጤት እያስመዘገበ ቢሆንም በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተጠናክሮ መሄድ እንዳለበት የገለፁት አቶ አበበ፤ የትምህርት ቤቶችን የውስጥ ገቢ ለማሳደግና ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ የተጀመረው ስራ በሁሉም ደረጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ በመናኸሪያዎች አካባቢ የሚፈጠሩ የአሰራር ክፍተቶችን ፈጥኖ በማረም ለህዝብ ተጠቃሚነት መስራት እንደሚገባ ገልፀው፤ የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለመፍታትና ህገወጥ አሰራሮችን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማሸነፍ ምርትና ምርታማነት መጨመር ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ የግብርና ተግባራትን በመደገፍ፤ የግብዓት አቅርቦት በማሻሻልና በቅንጅት ውጤታማ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በበጀት አመቱ በ6 ወራት የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስጠበቅ በቀጣይ ጊዜያት በሁሉም ዘርፎች የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አቶ አበበ አስገንዝበዋል።

ጉባኤው የተለያዩ አዋጆችን በማጽደቅና አቶ እምሩ ወየሳን የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አድርጎ በመሾም ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ ወንድማገኝ ገሪቶ – ከማሻ ጣቢያችን