በወልቂጤ ከተማ የተፈጠረውን ሰላም በዘላቂነት ለማፅናት የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ

በወልቂጤ ከተማ የተፈጠረውን ሰላም በዘላቂነት ለማፅናት የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ: መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወልቂጤ ከተማ የተፈጠረውን ሰላም በዘላቂነት ለማፅናት የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ማጠናከር እና የህዝብ ለህዝብ ተስስር እንዲዳብር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።

በከተማው ለግጭት ምክንያት የነበሩ ችግሮችን በመለየት የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸው ደግሞ በከተማው ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል ሲሉ ነዋሪዎች ገልፀዋል።

ሰላምን በሰላሙ ጊዜ መስራት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም የግጭት ችግሮችንና አዝማሚያዎችን በመረዳት የሰላም ባህልንም ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው። ታዲያ ይህንን የተረዱ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ለሰላማቸው ዘብ በመቆምና አለመግባባቶችን በመፍታት ከተማቸው ሰላም መሆኗን ተናግረዋል።

በከተማው ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴ በመፍታት የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲዳብር እየተሰራ መሆኑን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ተናግረዋል።

በከተማው ለግጭት ምክንያት የነበሩ ችግሮችንም በዘላቂነት ለመፍታት የክልል መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀናጀት የጥናት ቡድን ተዋቅሮ እየተሰራ ስለመሆኑም ከንቲባው አስረድተዋል።

በክልሉ ህዝቦች የተሟላ ሰላምና ልማት እንዳያረጋግጡ ከፋፋይ ትርክቶችን በማሰራጨት ህገ ወጥ ተግባር በሚሰሩ አካላት ላይ ክልሉ ህጋዊ እርምጃ በመውሰዱ ሰላምን ማፅናት ተችሏል ያሉት ደግሞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሐመድ ኑሪዬ ናቸው።

ዘጋቢ: ቴድሮስ ወርቅነህ