ቀናት በቀሩት ታላቁ የረመዳን ወር ሙስሊሙ ማህበረሰብ የመረዳዳትና የመተጋገዝ መልካም ስራዎችን ይበልጥ አጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸህ አደም መሀመድ አሳሰቡ

ቀናት በቀሩት ታላቁ የረመዳን ወር ሙስሊሙ ማህበረሰብ የመረዳዳትና የመተጋገዝ መልካም ስራዎችን ይበልጥ አጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸህ አደም መሀመድ አሳሰቡ

በእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ መሰረታዊ ከሚባሉት አምስቱ የዕምነቱ መሰረቶች መካከል የረመዳን ፆም አንዱ ነው።

የረመዳን ፆም ወር በእምነቱ አስተምህሮ ታላላቅ በረከቶችን የተጎናፀፈ የበዛ ምህረትና ዕዝነት ከፈጣሪ የሚገኝበት የተከበረ ወር መሆኑን የዕምነቱ መሪዎች ይናገራሉ።

በታላቁ የረመዳን ወር የዛሬው 27ኛ ሌሊት እጅግ ውድና የተለየ ስፍራ የሚሰጠው አንድ ተአምር ይዟል፡፡ ይህም ለይለቱል ቀድር ወይም የመወሰኛው ሌሊት በመባል ይጠራል።

በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ የሚገኘው የነስር መስጅድ ኢማምና የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሸህ አደም መሀመድ እንደተናገሩት፤ የረመዳን ወር እየተገባደደ ሲመጣ የመጨረሻዎቹ 10 ቀናት እጅግ ውድና ያልተጠበቀ አስደናቂ ነገርን ይዘዋል።

ይህችም ዕለት ለይለተል ቀድር ወይም የመወሰኛዋ ሌሊት ትባላለች።

ይህች ከሌሊቶች ሁሉ የተባረከችና እጅግ ውድ የሆነች ሌሊት በረመዳን ከመጨረሸዎቹ 10 ቀናት በአንዱ የምትከሰት ቢሆንም በአብዛኛው በ27ኛው ሌሊት የመከሰቱ ዕድል እንደሚኖር ሸህ አደም ይናገራሉ።

እንደዕምነቱ አስተምህሮ በዚች ውድ በሆነችው ሌሊት የተቀደሱ መላዕክት ከሰማየ ሰማያት በተደጋጋሚ ወደ ምድር ይወርዳሉ ይላሉ።

በዚች በተመረጠችው ተአምራዊ ሌሊት የተሰሩ ማንኛውም መልካም ስራዎች ከአንድ ሺህ ወራቶች በላይ ወይም ከ83 አመታት በላይ መልካም ስራ እንደሰራ የሚቆጠርለት በመሆኑ የተለየች ሌሊት ያደርጋታል ነው ያሉት።

ታዲያ ይህቺ ውድ ሌሊት ያጋጠመው ሰው እድለኛ ከመሆኑም በላይ በተለይ በዚህ ዘመን ካለው የሰው ልጅ እድሜና ስራው አንፃር ትልቅ የማካካሻ ወርቃማ እድል ተደርጐ ይታያል፡፡

በረመዳን ወር ከወትሮ በተለየ መልኩ ፍፁም የሆነ አንድነት፣ ወንድማማችነትና የጠነከረ አብሮነት ጐልቶ የሚታይ ሲሆን በተለይ አንዱ ለሌላው ያለው መተሳሰብና የመተዛዘን ስሜት በስፋት በመኖሩ ወሩን ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

የእምነቱ ተከታዮችም የቀሩትን ጥቂት ቀናት በጾምና በፀሎት ተግተው በማሳለፍ ፍፁም የሆነ ይቅርታና ምህረትን ከፈጣሪያቸው እንዲደረግላቸው ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባም ሸህ አደም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን