በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የተመራ የተቋሙ አመራሮች ቡድን በክልሉ በጉራጌ እና ስልጤ ዞኖች በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በጤና ተቋማት ደረጃ የፅዱ ኢትዮጵያ ትግባራ ያለበትን ደረጃ ምልከታ አድርጓል።
በጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ ቀቡል የገጠር ቀበሌ፣ የቋንጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እንዲሁም በስልጤ ዞን ምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ምዕራብ ሙጎ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘውን አይሳኮ አጠቃላይ የጤና ኬላ እና የሌራ ጤና ጣቢያዎች የተጎበኙ ሲሆን ከግለሰብ እስከ ተቋማት የጽዱ አካባቢ ትግበራ በምልከታው ተዳሷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረውን የፅዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቪ መነሻ በጤናው ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራትን በስፋት በማከናወን ጽዱ መንደር የመፍጠር ስራ እየተሰራ መሆኑን በምልከታው ወቅት የቢሮ ሃላፊው አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ተናግረዋል።
በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የቤተሰብ እና የመንገድ ዳር ሽንት ቤቶችን በማኖር ሜዳ ላይ ከመጸዳዳት ነጻ የሆኑ አካባቢዎችን የመፍጠርና እስከ ጤና ተቋማት ንጽህና መጠበቅን ከፅዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ጋር በማስተሳሰር እየተተገበረ ስለመሆኑ ሀላፊው ገልፀዋል።
በዚህም በንጽህና ጉድለት ሊከሰቱ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል የበሽታው መጠን እየቀነሰ ስለመምጣቱም ጠቅሰዋል።
በትግበራውም በክልሉ የሚገኙ 230 ጤና ጣቢያዎችን እና 31 ሆስፒታሎችን ጽዱና ሳቢ በማድረግ ለተገልጋዮች ምቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊው አሳውቀዋል።
ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሴቶች ልማት ህብረት ሚና የጎላ መሆኑን የገለጹት አቶ ሳሙኤል በጤና ሴክተሩ ክትትል፤ በየመዋቀሩ ድጋፍና በጤና ኤክስቴንሽኖች ባለቤትነት ከተመራ ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
የቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ ሜዳ ላይ መጸዳዳትን ማስቀረት የፅዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ አካል መሆኑን ገልጸው ይህም የማህበረሰቡን ትልቅ የባህሪ ለውጥ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ተግባሩን በዋናነት እየተወጣ ያለው የሴቶች ልማት ኅብረት የተሻሻለ መጸዳጃ ቤቶችን ከመገንባት ባለፈ ለንጽህና ግብይት ስርዓት የሚቀርቡ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማቸው የሚበረታታ እንደሆነ አንስተዋል።
በበጀት አመቱ በመጀመሪያው ግማሽ በሶስቱ ዞኖች በተመረጡ 3 ወረዳዎች ትግበራው መኖሩንና በቀሪ ጊዜያት ተጨማሪ ሶስት ወረዳዎች ላይ እንደሚጀመርም አሳውቀዋል።
በዞኑ የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነውንና አረንጓዴ ምንጣፍ በመባል የሚታወቀውን የጀፎረ መንገድ ለፅዱ መንደር መነሻ ሆኖ እያገለገለ መሆኑንም የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገልጸዋል።
ጎን ለጎንም ከግለሰብ መኖሪያ እስከ ጤና ተቋማት ፅዱ እና ምቹ መንደሮችን የመፍጠር እንዲሁም የአመጋገብ ስርዓቱም ጽዱ እንዲሆን ከሌማት ትሩፋት ጋር የማስተሳሳር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ጉብኝት በተደረገባቸው አካባቢዎች ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ንፁህ መንደርን ለመፍጠር በተሰራው ስራ ቀድሞ በስፋት ይከሰቱ የነበሩ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች እየቀነሱ በመምጣታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተጠቃሚነታቸው ሙሉ እንዲሆን የኤሌክትሪክ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና በጤና ተቋማት የሚስተዋለው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንዲቀረፍላቸውም ጠይቀዋል።
ጉብኝቱ በቀጣይ አራት ቀናት በሌሎች ዞኖችም የሚቀጥል መሆኑም ተገልጿል።
ዘጋቢ: ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የማህበረሰቡን አንድነት፣ ሠላምና ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
በክህሎት ፣ በቴክኖሎጂና በተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውድድር ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ
በሀገሪቷ ባለፉት 7 የለዉጥ አመታት የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለፁ