የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ የእንሰት ተከላ ሥራ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቆመ

በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ የእንሰት ተከላ ንቅናቄ “100 የእንሰት ችግኝ ለአንድ አርሶ አደር” በሚል ተካሂዷል።

በወረዳው ከ4 ሚሊዮን በላይ የእንሰት ችግኝ ተከላ እንደሚካሄድም ተመላክቷል።

በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ ገልቻ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ብርቅነሽ ጎበና፤ የእርሻ መሬት ቢኖራቸውም ባለቤታቸው በሕወይት ባለመኖሩ ምክንያት ለዓመታት በችግር መኖራቸውን አንስተው ዛሬ ላይ የገደብ ወረዳ አስተዳደር በንቅናቄ ማሳቸው ላይ የእንሰት ተከላ በማካሄዱ ምስጋናቸውን በደስታ ገልጸዋል።

በገደብ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የአደጋ ስጋት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ቤተልሔም ኃይሌ፤ ሴቶች በምግብ እራሳቸውን በመቻልም ሆነ በልማት ሥራ እኩል ተሳትፎ በማድረግ ኑሮ ማሻሻል እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

ከ1 መቶ 50 በላይ የእንሰት ችግኝ በማሳቸው ላይ መትከላቸውን የተናገሩት አርሶ አደር አድማሱ ጎበና፤ ከራሳቸው ባለፈ የመግዛት አቅም ለሌላቸው የችግኝ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በጌዴኦ ዞን የዛሬ 2 ዓመት የተጀመረው 1መቶ እንሰት ለ 1 አርሶ አደር ኢኒሼቲቭ በገደብ ወረዳ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን የእንሰት ችግኞችን ለመትከል እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የተናገሩት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ምትኩ፤ እንሰት በመትከል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የኑሮ ውድነት ችግርን ለመቅረፍ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የእንሰት ችግኝ የመግዛት አቅም የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍም ከተለያዩ አካላት ድጋፍ በማሰባሰብ ችግኝ ተገዝቶ መሰራጨቱንም አስተዳዳሪው ጠቅሰዋል።

እንደ ሀገር በጠቅላይ ሚኒስትሩ በምግብ እራስን መቻል በሚል የተጀመሩ የሌማት ትሩፋቶችን በ90 ቀናት ዕቅድ የአሳ፣ ወተት፣ እንቁላልና ስጋ መንደር ለማቋቋም እንደሚሠራም አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል።

ዘጋቢ: ውብሸት ካሣሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን