ሀዋሳ፡ የካቲት 08/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ የበለፀገ ህብረተሰብ መፍጠር እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልፅግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ግርማ ባሻ ገለፁ፡፡
ይህን ያሉት “ሕብረብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በማሻ ከተማ በተካሄደው የህዝብ ውይይት ላይ ነው።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት በክልሉ ብልፅግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ግርማ ባሻ በክልል ደረጃ የተዘጋጀ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን የውይይት መድረኩ በዋናነት መንግስትና ህዝብ በጋራ በመሆን ያሉትን መልካም ለውጦች በማስቀጠል ተግዳሮቶች ላይ የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ እስከአሁን የነበሩ ስኬቶችን ማስቀጠልና መጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።
ሀብት ማፍራት ወሳኝ በመሆኑ ህዝብና መንግስት በጋራ በመሆን ሀገራችንን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ ያስፈልጋል፤ ይህም በፍትሃዊነትና በቅንነት መሆን አለበት ነው ያሉት።
የበለፀገ ህብረተሰብ ለመፍጠር ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ፣ አካባቢን ለኑሮ ምቹ ማድረግ እንዲሁም የስራ አጥነት ችግርን መቅረፍ እንደሚገባ አቶ ግርማ ጠቁመዋል።
በእጃችን ያለውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ሀገራችንን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ አለብን ያሉት አቶ ግርማ ውሃ፣ ማዕድን፣ ወርቅ፣ የሰው ሀይል አቅም መኖር ትልቅ የመልማት አጋጣሚ እንደሆነም ተናግረዋል።
ሀገራችን በብዙ ፈተና ውስጥ ሆና የሀገር ክብር በማስጠበቅ ሉአላዊነቷን ማስቀጠል፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከውድቀት የሚታደግ ስራ በለውጡ መንግስት የተሰራ መሆኑ፣ የዜጎችን ክብር የሚያስጠብቁ ስራዎች እየተሠሩ በመሆናቸው ለውጦች እየታዩ ይገኛሉ ብለዋል።
በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ የቆዩ እዳዎች መኖራቸው፣ ያልሰለጠነ የፖለቲካ ባህል መኖር፣ ገለልተኛ ተቋማት ያለመፍጠር ችግር፣ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት መኖር ለሀገራችን ትልቅ ተግዳሮት ሆነዋል ነው ያሉት።
ከዚህ ችግር ለመውጣት በወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በማጠናከር በአብሮነት መንፈስ ሀገራችንን የበለፀገች ማድረግ አለብን ብለዋል።
ሀብት መፍጠር ብቻ ሳይሆን ሀብት በተገቢው መያዝ አስፈላጊ እንደሆነ የገለፁት አቶ ግርማ ሀገራችን ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ሆና ብዙ ድሎችን በተለያዩ ዘርፎች ላይ እያስመዘገበች በመሆኗ ህብረብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በማጠናከር የበለፀገች ኢትዮጵያን መፍጠር ከሁላችንም ይጠበቃል በማለት አብራርተዋል።
ለውይይቱ ተሳታፊዎች በከተማ ደረጃ የተዘጋጀ ሰነድ ያቀረቡት የማሻ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰራዊት አየነው እንደገለፁት የከተማ ነዋሪዎች የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው የቆዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ጠቁመዋል።
በዚህም መሬትን በበቂ ሁኔታ አዘጋጅቶ የማስተላለፍ ውስንነት፣ ቆሻሻን በቆሻሻ መጣያ ቦታዎችን በወቅቱ አለመጣል፣ ህገ ወጥ ግንባታ ቁጥጥር ያለማድረግ፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል በበቂ ሁኔታ ያለመፍጠር፣ የመድሀኒት እጥረት እና የትምህርት ግብዓት ያለማሟላት የከተማ ህዝብ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የከተማውን ህዝብ ተሳታፊ ያደረገ የከተማ ልማት ሥራ በመሠራቱ በከተማ መሠረተ ልማትና በሌሎችም ማህበራዊ ዘርፎች አዎንታዊ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም ጭምር ተናግረዋል።
የክልል አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ሀላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ በበኩላቸው ከእዳ ወደ ምንዳ በመሻገር ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁላችንም በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክር ሳይደረግ መጓተት፣ በመንግስት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መኖር፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ያለመኖር፣ የመንግስት ሰራተኞች የጤና መድህን ተጠቃሚ እንዳይሆኑ መደረጉ ተገቢ ያለመሆኑ እንዲሁም ዞኑ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ ቢሆንም የተፈለገውን ያህል ውጤታማ ያለመሆኑን እንደ ችግር አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ እንደ ክልል የመጻህፍት ህትመት መዘግየት እንዲሁም አንድን መፅሐፍ 8 ያህል ተማሪዎች እየተጋሩ ባሉበት የትምህት ጥራት ማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ውይይቱን የመሩት የዞንና ክልል እንዲሁም የከተማ አስተዳደር አመራሮች በተሳታፊዎች በተነሳሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራርያ በመስጠት ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና ለሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ወንድማገኝ ገሪቶ – ከማሻ ጣቢያችን
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ