የክልሉ ጤና ቢሮ በሽታው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የተወሰዱ እርምጃዎች እና የተገኙ ውጤቶችን በሆሳዕና ከተማ ገምግሟል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ጤና የሁሉ ልማቶች መሠረት ነው፡፡ የጤና ዘርፍ ውጤታማ መሆን ከቻለ ሌሎች የልማት መስኮችን ማሳካት ከባድ አይሆንም።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን፤ የኩፍኝ ወረርሽኝ በሽታ ምልክቶች በኢትዮጵያ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን፣ በስልጤ ዞን፣ በሀዲያ ዞን፣ በሀላባ ዞን እና ጠምባሮ ልዩ ወረዳ መታየቱን ተናግረዋል።
በሽታውን ለመከላከል በተደረገው ጥረትም ከሀዲያ ዞን ከተወሰኑ ወረዳዎች በስተቀር በቁጥጥር ስር መዋሉን አመልክተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ህፃናት ለሽታው ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን አንስተው ለተጠቂዎቹ አፋጣኝ ህክምና መስጠት ካልተቻለ ጉዳቱ እስከሞት የደረሰ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
በልጅነት ወቅት የሚሰጡ መሠረታዊ ክትባቶችን በአግባቡ አለመውሰድ፣ የተሰጡ ክትባቶች በተለያዩት ምክንያቶች ጥራት መጓደል እና መሰል ችግሮች ለበሽታው መከሰት ምክንያት ሆኖዋል ይላሉ ዋና ዳይሬክተሩ።
በሽታውን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት አወንታዊ ሚና የተጫወቱ አካላትን አቶ ማሙሽ አመስግነዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ለገሠ ጴጥሮስ በበኩላቸው የኩፍኝ በሽታ በትንፋሽ የሚተላለፍ አደገኛ በሽታ መሆኑን ጠቅሰው ምልክቱ የታየባቸውን ሰዎች በአፋጣኝ በመለየት የህክምና ዕርዳታ መስጠት ይገባል ብለዋል።
ትኩሳት፣ ሰውነት ላይ የሽፍታ መከሰትና በአፍንጫ በኩል ከመደበኛው በዛ ያለ ፈሳሽ መውጣት የኩፍኝ በሽታ ምልክቶች ናቸው ይላል ምክትል ዳይሬክተሩ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ1 ሺ 7 መቶ 50 የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በበሽታው ተይዘው ወደ ህክምና ማዕከላት ገብተው ዕርዳታ ያገኙ ሲሆን አብዛኞቹ አገግመው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን የጠቀሱት ዶክተር ለገሠ ፤ የ15 ዜጎች ህይወት መቅጠፉንም አመልክተዋል።
የሀላባ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ግዛቸው፤ የሀላባ ዞን የኦሮሚያን ክልል ጨምሮ ከአጎራባች አካባቢዎች ህክምና ፍለጋ ወደ ቁሊቶ ጠቅላላ ሆስፒታል ስለሚመጡ ለበሽታው መዛመት ምክንያት እንዳይሆን ጥንቃቄ እያደረግን ነው ብለዋል።
የህክምና አገልግሎት ለሁሉም ዜጋ መስጠት ግዴታችን ቢሆንም ከአቅማችን በላይ እየሆነ በመምጣቱ የክልሉ ብሎም የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ: ጀማል የሱፍ
More Stories
የህብረተሰቡን ጤና ለማጎልበት የዘርፉን ተግባራት በተገቢው ለማሳካት ከምንጊዜውም በተሻለ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
የህዝቡን የልማት ፍላጎቶች ለማሟላትና መንግስታዊ አገልግሎቶችን በተገቢው ለመስጠት የውስጥ ገቢ ግብርን አማጦ ለመሰብሰብ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በይፋ ተጀመረ