ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ጥር 08/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተመልክቷል።
በጌዴኦ ዞን የይርጋ ጨፌ ከተማ አስተዳደር “ባለ ብዙ ፀጋ ከተሞቻችን በነዋሪዎች ተሳትፎና ባለቤትነት ወደ ብልጽግና ተምሳሌትነት” በሚል መሪ ቃል ከተማ አቀፍ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ መክፈቻ የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን ከተማውን ለማዘመን በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በከተሞች ያለውን ጤናማ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማፋጠን የመንገድ ከፈታ በህብረተሰብ ተሳትፎ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ከንቲባው፥ ከተሞችን በፕላን ማልማት ለቀጣይ ዕድገት ወሳኝነት እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ከተማውን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝነት እንዳለው የተናገሩት አቶ ታደለ፥ በህዝብ ተሳቶፎ የተጀመሩ ከተማ የማስፋፋት ሥራ፣ በመንግሥትና በባለሀብት ተሳትፎ የተጀመሩ ግንባታዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ውብ ከተማ ለመፍጠር በሚደረገው ርብርብ የከተማው ነዋሪዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለዚህም ከተማ አቀፍ የነዋሪዎች መድረክ መዘጋጀቱን ጠቅሰው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሁሉም ለተፈጻሚነቱ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበባየሁ ኢሳይያስ የከተሞችን ዕድገት ለማፋጠን የዞኑ አስተዳደር ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ከተሞች ቀጣይነት ያለውን ዕድገት እንዲያስመዘግቡ ጠንካራ አመራር መከተል አስፈላጊ መሆኑን አውስተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ በሁሉም አከባቢዎች በርካታ ምቹ ዕድሎች መኖራቸውን በመጠቆም፥ እኚህ ፀጋዎችን በአግባቡ መጠቀም በከተሞች ዘላቂ ዕድገት እንዲመጣ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
የይርጋጨፌ ከተማ ከዕድሜው አንጻር አለማደጉን የገለጹት አቶ ወገኔ፥ በአሁኑ ሰዓት የተጀመሩ መነቃቃቆችን አጠናክሮ በማስቀጠል በነዋሪዎች ተሳትፎና ባለቤትነት ስሜት ወደ ብልጽግና ተምሳሌትነት በማሳደግ ነገ የተሻለ ከተማ ለማድረግ መረባረብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የማህበረሰቡን አንድነት፣ ሠላምና ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
በክህሎት ፣ በቴክኖሎጂና በተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውድድር ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ
በሀገሪቷ ባለፉት 7 የለዉጥ አመታት የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለፁ